“በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ እንደ በጎ ፈቃዱ መፈለግንና ማድረግን በእናንተ ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና።” (ፊልጵስዩስ 2፥12)
እዚህ ክፍል ላይ ዋናው እና ወሳኙ ሠራተኛ እግዚአብሔር ነው። መፈለጉንም፣ መሥራቱንም የሚያደርገው እግዚአብሔር ስለሆነ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ ይለናል። እግዚአብሔር የወደደውን ለበጎ ፈቃዱ ይሠራል። ሆኖም ግን፣ ክርስቲያኖች ይህንን ያምናሉ ማለት ቁጭ ብለው ያያሉ ማለት አይደለም። ይልቁንም በተስፋ የተሞሉ ብርቱ እና ደፋር ሰዎች ያደርጋቸዋል።
እያንዳንዳችን በየዕለቱ የምንሰራው ልዩ ልዩ አገልግሎት አለን። ጳውሎስ ሥራውን እንድንሠራ ያዘናል። ነገር ግን ሥራውን መስራት ያለብን እግዚአብሔር በሚሰጠው ኃይል እንደሆነም ይነግረናል። ይህም ደግሞ የሚሆነው እርሱን በማመን ነው። እመኑት! በዚህ ቀን እግዚአብሔር በእናንተ ውስጥ ለበጎ ፈቃዱ መፈለግንና ማድረግን እንደሚሠራ የተናገረውን የተስፋ ቃል እመኑ።
በዕለት ተዕለት ኑሯችን እና ልምምዳችን ውስጥ የሚያስፈልገንን ጸጋ የሚያቀርበው ራሱ እግዚአብሔር ነው። ጳውሎስ መዳናችንን እንዴት እንደምንፈጽም ሲያብራራ፣ የሚያተኩረው ያለፈውን ጸጋ በማመስገን ላይ አይደለም። ይህን ያነሣሁት ብዙ ክርስቲያኖች የታዛዥነታቸው ምክንያት ምን እንደሆነ ሲጠየቁ፣ ስለተደረገላቸው ነገር የምስጋና ምላሽ መሆኑን ይናገራሉ። ነገር ግን ጳውሎስ ስለ ሥራችን ተነሣሽነት እና ኃይል ሲናገር አጽንዖት የሰጠው ውለታ መላሽነት ላይ አይደለም። ላለፈው ነገር ለማመስገን ብቻ አይደለም። የጳውሎስ ትኩረት እግዚአብሔር በፊት ባደረጋቸው ነገሮች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ገና በሚያደርጋቸው ነገሮች ላይ ባለ እምነት ነው። መዳናችሁን ፈጽሙ! ለምን? እንዴት? ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእያንዳንዱ ቅጽበት የሚሆን አዲስ ጸጋ ስላለ። በፈለጋችሁ እና ባደረጋችሁ ቁጥር በእናንተ መፈለግ እና ማድረግ ውስጥ እየሠራ ያለው ራሱ እግዚአብሔር ነው። ይህን እውነት አጥብቃችሁ ያዙ። በቀጣዩ ሰዓትም ሆነ በሚቀጥሉት ሺህ ዓመታት ለሚመጡ ተግዳሮቶች ይህንን እውነት እመኑ።
ወደፊት በሚገለጠው የጸጋ ኃይል የምናገኘው የሕያው ክርስቶስን ኃይል ነው። ይህም በእያንዳንዱ አዳዲስ የሕይወታችን መስክ ውስጥ ሁሉ ለእኛ እና በእኛ ውስጥ ይሠራል። ስለዚህም ጳውሎስ ከእርሱ ጋር የነበረው የእግዚአብሔር ጸጋ ያስከተለውን ውጤት ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “በተናገርሁትና ባደረግሁት ነገር አሕዛብ ለእግዚአብሔር እንዲታዘዙ፣ ክርስቶስ በእኔ ሆኖ ከፈጸመው በቀር ሌላ ነገር ለመናገር አልደፍርም” (ሮሜ 15፥18)።
ስለዚህ ጳውሎስ፣ ክርስቶስ በአገልግሎቱ ካከናወነው በቀር ስለ ምንም ነገር ሊናገር ካልደፈረ፣ ነገር ግን ጸጋው በአገልግሎቱ ያከናወነውን ከተናገረ (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥10)፣ ያ የጸጋው ኃይል የክርስቶስ ኃይል መሆን አለበት ማለት ነው። ጸጋ የክርስቶስ ኃይል ነው።
ይህም ማለት በሚቀጥሉት አምስት ደቂቃዎችም ሆነ በሚቀጥሉት ሃምሳ ዓመታት ለሚኖረን አገልግሎት ኀይልን የምናገኘው ሁሉን ቻይ ከሆነው የክርስቶስ ጸጋ ነው። ይህ ጸጋ ሁልጊዜም ከእኛ ጋር እንደሚሆን ቃል ተገብቶልናል። ለበጎ ፈቃዱም መፈለግን እና ማድረግን በእኛ ውስጥ ይሠራል።