በሙላቱ መደሰት | የካቲት 23

ከእርሱ ሙላት ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀብለናል። (ዮሐንስ 1፥16)

ያለፈው እሁድ ልክ የአምልኮ ፕሮግራም ከመጀመሩ በፊት፣ የተወሰኑ የቤተ ክርስቲያናችን ምዕመናን፣ ስለ ሕዝባችን እንዲሁም በከተማችን ስለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት፣ ደግሞም በአጠቃላይ ስለ አገራችን ሕዝብ እምነት እየተጋደሉ ሲጸለዩ ነበር። ከመካከላቸውም አንድ ሰው በዮሐንስ 1፥1416 ላይ ያሉትን ቃላት ጸለየ፦

ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም አደረ፤ እኛም ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ ከአባቱ ዘንድ የመጣውን የአንድያ ልጅን ክብር አየን። … ከእርሱ ሙላት ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀብለናል

ትልቅ ትምህርትን ከተማርኩባቸው አጋጣሚዎች መካከል ይህ አንዱ ነበር። በዚያች ደቂቃ “ከእርሱ ሙላት” የሚለው ሐሳብ ልዩ በሆነ መልኩ ተሰማኝ። ይህ ቃል የያዘው እውነታ ምን ያህል ክብደት እንዳለው መረዳት ቻልኩ። ያም ሙላት በእርግጥ የክርስቶስ ሙላት ነው።

በእርግጥም ከእርሱ ሙላት በጸጋ ላይ ጸጋን እንደተቀበልሁ ገባኝና ተደነቅሁ። በዚያች ቅጽበትም እንኳ በጸጋ ላይ ጸጋን እየተቀበልኩ ነበር። ወዲያውኑም ቀኑን ሙሉ በእግሮቹ ሥር በመቀመጥ ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነቡ በመዋል የእርሱን ሙላት መትረፍርፍ ከማጣጣም የበለጠ ጣፋጭ ነገር እንደሌለ ተረዳሁ።

ለምንድን ነው ይህ ሙላት ጥልቅ ተጽእኖ ያሳደረብኝ? ለምንስ ነው እስካሁን ባልለመድኩት መልኩ እየተሰማኝ ያለው? ብዙ ምክንያቶች አሉኝ …

  • . . . ከሙላቱ በጸጋ የምረሰርስበት እርሱ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ቃል ነው። ደግሞም እራሱ እግዚአብሔር ነው (ዮሐንስ 1፥1-2)። ስለዚህም መለኮታዊ እና ማብቂያ የሌለው የእርሱ ሙላት የእግዚአብሔር ሙላት ነው።
  • . . . ይህም ቃል ስጋን ለበሰ። ከእኛም እንደ አንዱ ሆነ። በሙላቱም እኛን አጥብቆ ፈለገን። ይህም ሙላት ሊደረስበት የሚችል ሙላት ነው።
  • . . . ይህም ቃል በሰው መልክ ተገለጠ፤ ክብሩም ታየ። የእርሱ ሙላት እጅግ የከበረ ሙላት ነው።
  • . . . ይህም ቃል “ከአባቱ ዘንድ የመጣው አንድያ ልጅ” ነው (ዮሐንስ 1፥14)። ስለዚህም ያ መለኮታዊ ሙላት ወደ እኔ ይመጣ የነበረው ከእግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር በኩል ነው። እግዚአብሔር አንድን መልአክ ሳይሆን ብቸኛ ልጁን ሙላቱን እንዲገልጥ ልኳል።
  • . . . የልጁ ሙላት የጸጋ ሙላት ነው። ይህም ሙላት የሚያሰምጠን እና የሚያጠፋን ሳይሆን በሁሉ መንገድ የሚባርከን ነው።
  • . . . ይህ ሙላት የጸጋ ሙላት ብቻ ሳይሆን እውነት የሞላበትም ነው። እውነት በሌለው የሽንገላ ንግግር የተሞላ አይደለም። ይህ ጸጋ በጸና አለት ላይ የተመሠረተ እውነታ ነው።

ታዲያ በክርስቶስ ሙላት ብደነቅ፣ ከዚያም አልፎ ደግሞ ሐሴትን ባደርግ ምን ይገርማል?