ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? ችግር ነው ወይስ ሥቃይ፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ረሀብ፣ ወይስ ዕራቍትነት፣ ወይስ አደጋ ወይስ ሰይፍ? (ሮሜ 8፥35)
በሮሜ 8፥35 ያሉትን እነዚህን ሦስት ነገሮች እንመልከት።
- ክርስቶስ አሁንም እየወደደን ነው።
አንዲት ሚስት ስለሞተው ባሏ ስትናገር “ከፍቅሩ ምንም ነገር አይለየኝም” ብትል፣ የፍቅሩ ትዝታ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ጣፋጭ እና ኃይለኛ ሆኖ ይኖራል እያለች ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ጳውሎስ እዚህ ጋር እያለ ያለው እንደዚያ አይደለም።
በሮሜ 8፥34 ላይ በግልፅ “የሞተው፣ እንዲሁም ከሞት የተነሣው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠው ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ስለ እኛ ይማልዳል” ይላል። ጳውሎስ ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ምንም ነገር የለም ሊል የቻለበት ምክንያት ክርስቶስ ሕያው ስለሆነ እና አሁንም እየወደደን ስለሆነ ነው።
እርሱ በእግዚአብሔር ቀኝ ነው፤ ስለእኛም እየገዛልን ነው። እርሱም ስለ እኛ ይማልዳል፣ ይህ ማለት የፈጸመው የቤዛነት ሥራ ያለማቋረጥ እንዲያድን እና በደህና ተጠብቀን ወደ ዘላለማዊ ደስታ እንዲያመጣን እየሰራ ነው። ፍቅሩ ያለፈ ትዝታ ብቻ አይደለም። ሁሉን ቻይ በሆነው፣ ወደ ዘላለማዊ ደስታ ሊወስደን በሚችለው በእግዚአብሔር ልጅ የሚሰራ የሁልጊዜ ጊዜ ስራ ነው።
- ይህ የክርስቶስ ፍቅር እኛን ከመለያየት በመጠበቅ ረገድ ውጤታማ ነው፤ ስለዚህም ለዓለም ሁሉ የሆነ ፍቅር አይደለም። ነገር ግን የተለየ ለሕዝቡ ያለው ፍቅር ነው – ማለትም በሮሜ 8፥28 መሰረት እግዚአብሔርን ለሚወዱትና እንደ ሐሳቡ ለተጠሩት ነው።
በኤፌሶን 5፥25 ያለው ፍቅር ይህ ነው፦“ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ፣ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ።” ክርስቶስ ለሙሽራው ለቤተ ክርስቲያን ያለው ያ ፍቅር ነው። ክርስቶስ ለሁሉም ፍቅር አለው፤ ደግሞም ለሙሽራው ልዩ የሆነ የሚያድን፣ የሚጠብቅ ፍቅር አለው። የዚህች ሙሽራ አካል እንደሆናችሁ የምታውቁት ክርስቶስን የምታምኑ ከሆነ ነው። በክርስቶስ የሚያምን ማንም ሰው፣ ማንም ቢሆን ማንም፣ “እኔ ሙሽራው የሆነችው የቤተ ክርስቲያን አካል ነኝ፣ የተጠራሁ እና የተመረጥሁ ነኝ፣ በሮሜ 8፥35 መሠረት፣ ምንም ቢሆን ለዘላለም የተጠበቅሁ ነኝ” ማለት ይችላል።
- ይህ ሁሉን ቻይ የሆነና አዳኝ የሆነ ፍቅር በዚህ ሕይወት ውስጥ ካሉት መከራዎች ሙሉ በሙሉ ባያድነንም፤ በመከራ ሁሉ መካከል በደህና አሳልፎ ወደ ዘላለማዊው የእግዚአብሔር ደስታ ግን ያደርሰናል።
ሞት ይደርስብናል፤ ነገር ግን አይለየንም። ይህንን ነው ጳውሎስ እያለ ያለው። ሰይፍ ከክርስቶስ ፍቅር እንደማይለየን ሲናገር፣ ብንገደልም እንኳን ከክርስቶስ ፍቅር አንለይም ማለቱ ነው።
ስለዚህ በቁጥር 35 ላይ ያለው አጠቃላይ ሀሳብ ይህ ነው፦ ኢየሱስ ክርስቶስ በአሁኑ ጊዜ ልጆቹን ሁሉ በየደቂቃው ያለማቋረጥ ሁሉን ቻይ በሆነ ፍቅር እየወደደ ይገኛል። ይህ ፍቅር ከሁሉም መከራ ባይጋርደንም፣ በመከራም ሆነ በሞት መካከል በፊቱ ዘላለማዊ ደስታን እንድናገኝ ይጠብቀናል።