የቀራንዮ የፍቅር እርምጃ | የካቲት 16

ሕይወቱን ስለ እኛ አሳልፎ ስለ ሰጠ፣ ፍቅር ምን እንደሆነ በዚህ እናውቃለን። (1 ዮሐንስ 3፥16)

የኢየሱስ የመስቀል ሞት አስቦበት የጠጣው ጽዋ ነው። ሞቱ ብቻ ሳይሆን፣ የተቀበለው እያንዳንዱ መከራ በዓላማ የተደረገ እና ለእኛ ያለው ፍቅርም ከጅማሬው የታየበት ነበር። አውቆ እና አቅዶበት ሕይወቱን የሰጠው ደግሞ ስለእኛ ሲል ነው። ፍቅር ደግሞ ያ ነው።

“ኢየሱስም ይህን ዓለም ትቶ ወደ አብ የሚሄድበት ጊዜ እንደ ደረሰ ዐወቀ። በዓለም የነበሩትን፣ የራሱ የሆኑትን ወደዳቸው፤ በፍጹም ፍቅሩም ወደዳቸው” (ዮሐንስ 13፥1)።

ከቀራንዮ እያንዳንዱ እርምጃ ጀርባ “እወድዳችኋለሁ” የሚል ድምጽ አለ።

ስለዚህ፣ ክርስቶስ ሕይወቱን በፈቃዱ አሳልፎ በመስጠት የገለጠውን ፍቅሩን መረዳት፣ ምን ያህል አስቦበት እንዳደረገው ለመመልከት ይረዳል።

ጴጥሮስ ኢየሱስን ሊይዙት ከመጡት ሰዎች መካከል የአንዱን አገልጋይ ጭንቅላት በስለት ለመሰንጠቅ ሞክሮ ሲስትና ጆሮውን ብቻ ሲቆርጠው ወዲያውኑ ኢየሱስ ያለውን ተመልከቱ፦

“ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ ‘በል ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍን የሚመዝዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ። ካስፈለገ አባቴን ብለምነው ከዐሥራ ሁለት ክፍለ ሰራዊት የሚበልጡ መላእክት የማይሰድልኝ ይመስልሃል? ይህ ቢሆን ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍት ይሆናል ያሉት ነገር እንዴት ይፈጸማል?’” (ማቴዎስ 26፥52-54)

የኢየሱስ ሞት በብሉይ ኪዳን ውስጥ ተተንብዮ ነበር ማለት አንድ ነገር ነው። ከዚህ ይልቅ የሚገርመው፣ ኢየሱስ እያንዳንዱን ውሳኔ ሲወስን ቅዱሳት መጻሕፍት ፍጻሜን ያገኙ ዘንድ በመጠንቀቅ ነበር ማለት ነው።

ማቴዎስ 26፥54 ላይም ኢየሱስ ያለው ይህንኑ ነው፦ “ይህንን ስቃይ ላልፈው እችላለሁ፤ ግን ይህ ቢሆን ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍት ይሆናል ያሉት ነገር እንዴት ሊፈጸም ይችላል?”

በሌላ አገላለጽ ኢየሱስ እ ያለ ያለው ይህንን ነው፦ የእግዚአብሔርን ቃል ስለማውቅ፣ ይህንን መከራ ማምለጥ ብችልም እንኳ የማመልጥበትን መንገድ አልመርጥም። ሕዝቤ ይድን ዘንድ ምን መደረግ እንዳለበት ስለማውቅ፣ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ስለ እኔ የተተነበየውን ሁሉ መፈጸምን መርጫለሁ። በእያንዳንዱ እርምጃዬ የእኔ የሆኑትን እስከመጨረሻው ለመውደድ መርጫለሁ። ይህም ደግሞ በእርግጠኝነት እንዲሰማቸው፣ ነጻ እንዲሆኑ እና ከዓለም ፍጹም የተለዩ እንዲሆኑ እፈልጋለሁ።