“የዚህ ትእዛዝ ዓላማ ግን ከንጹሕ ልብ፣ ከበጎ ኅሊና እንዲሁም ከእውነተኛ እምነት የሚገኝ ፍቅር ነው።” (1ኛ ጢሞቴዎስ 1፥5)
ጳውሎስ ፍቅርን ዓላማው አድርጓል። የዚህ ታላቅ ውጤት ምንጭ ከሆኑት መካከል አንዱ እውነተኛ እምነት ነው። እምነት የፍቅር ምንጭ የሆነበት ምክንያት፣ በእግዚአብሔር ጸጋ አማካይነት ፍቅርን የሚከለክለውን የኃጢአት ኃይል ከልባችን ስለሚያስወግድ ነው።
የጥፋተኝነት ስሜት ከተሰማን፣ ለሌላ ሰው ግድ መሰኘት በማንችልበት መልኩ ራስ ተኮር በሆነ ጭንቀትና ሐዘን ውስጥ እንዋጣለን፤ ማየትም ይሳነናል። ክሱንና የጥፋተኝነት ስሜቱን ለመሸፈን ግብዞች እንሆናለን፤ ስለዚህም በግንኙነቶቻችን ውስጥ ያለውን እውነተኝነትንና ቅንነትን ሁሉ እናጠፋለን። ይህም ሁኔታ እውነተኛ ፍቅር እንዳይኖር ያደርገዋል። ወይም ደግሞ የራሳችንን ጥፋት ለመደበቅ ስንል የሌሎችን ጥፋት እናወራለን። ይህ ግን የፍቅር ባሕሪ አይደለም። ስለዚህ መውደድን ከፈለግን አውዳሚ የሆነው የጥፋተኝነት ስሜት ተጽዕኖ መሸነፍ አለበት።
ፍርሃትም እንደዚሁ ነው። ውስጣችን በፍርሃት ከተሞላ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንድንቀበላቸው እና እንድናበረታታቸው የሚገባቸውን እንግዶች መቅረብ አንፈልግም። ወይም ደግሞ አደጋ የበዛበትን የወንጌል ተልዕኮ እንደ ጥሪ ላንቀበለው እንችላለን። አልያም ከመጠን በላይ የሆነ ገንዘብ ለዋስትና ኩባንያዎች ልናጠፋ እንችላለን፤ ወይም ደግሞ በራሳችን ጉዳይ በመጠመድ፣ የሌሎችን ፍላጎት እንዳንመለከት በሚያደርጉ ጥቃቅን ፍርሃቶች ልንዋጥ እንችላለን። እነዚህ ሁሉ የፍቅር ተቃራኒዎች ናቸው።
ስግብግብነትም እንዲሁ ነው። ስግብግብ ከሆንን ለወንጌል መስፋፋት መዋል የሚገባውን ገንዘብ በቅንጦት ላይ እናውለው ይሆናል። የእኛ ትክክለኛ ይዞታ እና የወደፊት የገንዘብ አቅማችን አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ምንም ዐይነት ዋጋ የሚያስከፍለን ነገር አናደርግም። ከሰዎች ይልቅ ነገሮች ላይ እናተኩራለን፤ ወይም ሰዎችን ለቁሳዊ ጥቅማችን ብቻ ስንል እንደ ግብዓት እናያለን። ስለዚህም ፍቅር ዋጋውን ያጣል።
ወደፊት በሚገለጠው ጸጋ ላይ ያለ እምነት ግን ጥፋተኝነትን፣ ፍርሃትንና ስግብግብነትን ከልብ በማውጣት ፍቅርን ይፈጥራል።
የክርስቶስ ሞት ለአሁንና ለዘላለም ጻድቅ ማድረግ ይችላል’ የሚለውን ተስፋ አጥብቆ ስለሚይዝ የጥፋተኝነት ስሜትን ያስወግዳል (ዕብራውያን 10፥14)።
“እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ። አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ” በሚለው ተስፋ ላይ ስለሚታመን ፍርሃትን ይስወግዳል (ኢሳይያስ 41፥10)።
ይህ እምነት፣ ክርስቶስ ዓለም ሁሉ ሊሰጠው ከሚችለው ሀብት ሁሉ የላቀ መሆኑን እርግጠኛ ስለሆነ፣ ስግብግብነትንም ያስወግዳል (ማቴዎስ 13፥44)። ስለዚህ ጳውሎስ፣ “የዚህ ትእዛዝ ዓላማ ግን ከንጹሕ ልብ፣ ከበጎ ኅሊና እንዲሁም ከእውነተኛ እምነት የሚገኝ ፍቅር ነው” ሲል ለመውደድ እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ማሸነፍ ስለሚችለው ታላቅ የእምነት ኃይል እየተናገረ ነው። የእምነትን ገድል ስንጋደል የምንጋደለው፣ ስግብግብነትን፣ ፍርሃትን እና ክስን ሁሉ ባስወገደ በእግዚአብሔር ተስፋ ለማመን ነው፤ ይህም ተጋድሎ የፍቅር ተጋድሎ ነው።