በእግዚአብሔር የተሰጡ ተስፋዎች ሁሉ፣ “አዎን” የሚሆኑት በእርሱ ነውና። (2ኛ ቆሮንቶስ 1፥20)
“በእግዚአብሔር የተሰጡ ተስፋዎች ሁሉ፣ ‘አዎን’ የሚሆኑት” በኢየሱስ ከሆነ፣ አሁን ላይ እርሱን ማመን ማለት የተናገረው የተስፋ ቃል ሁሉ እውን እንደሚሆን ማመን ነው ማለት ነው።
እርሱን ማመን እና ተስፋዎቹን ማመን ሁለት የተለያዩ እምነቶች አይደሉም። ለመዳናችን ኢየሱስን ማመን ቃሉን እንደሚጠብቅ ማመን ማለት ነው። በተሰቀለውና ከሞት በተነሳው ኢየሱስ መርካት፣ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ለዘላለም፣ አንድም ነገር ከፍቅሩ እንደማይለየን ወይም ነገር ሁሉን አያይዞ ለበጎ ከመሥራት ምንም እንደማይከለክለው ማመንን ያካትታል። ይህም የሚሠራልን በጎ በጎ ነገር ከሁሉም በላይ በክርስቶስ በኩል ያለውን የእግዚአብሔርን ውበት እና ክብር እንደ ውዱ ሃብታችን ማየት እና ማጣጣም ነው።
ይህ ፍጹም የሚያረካ በጎ ነገር ለዘላለም ለእኛ እንደሚሆን እርግጠኛ የምንሆነው፣ አስቀድመን ባየነው ክቡር ጸጋው ላይ መሰረት አድርገን ነው። በተለይም እግዚአብሔር ለገዛ ልጁ ሳይሳሳለት፣ ነገር ግን ለሁላችንም አሳልፎ በሰጠው ጸጋ ላይ የተመሠረተ ነው (ሮሜ 8፥32)።
ባለፉት አስደናቂ ሥራዎቹ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን መንፈሳዊ ውበት ልንቀምስ ያስፈልገናል። በተለይም ለኃጢአታችን በሆነው የክርስቶስ ሞት እና ትንሳኤ እንዲሁም በተስፋ ቃሎቹ ሁሉ ያገኘነው እጅግ የሚደንቅ ነገር ነው። በዚህ አስቀድመን ባየነው ጸጋ ላይ ተመሥርተን፣ በሚቀጥለው ወር፣ በሚቀጥለው የሕይወታችን ምዕራፍ፣ ብሎም ማለቂያ ለሌለው ዘላለም፣ እግዚአብሔር ራሱ ለእኛ በሚሆንልን ነገር ሁሉ ላይ በእርግጠኝነት እና በእምነት እንደላደል።
ነፍሳችንን ወደፊት የሚያረካው እርሱና እርሱ ብቻ ነው። እናም ክርስቶስ እንድንኖር የጠራንን ቆራጥ ክርስቲያናዊ ሕይወት እዚህ እና አሁን መኖር ከፈለግን፣ ወደፊት ፍጹም እንደሚያረካን እርግጠኛ መሆን አለብን።
አሁን ላይ በክርስቶስ ያለን ደስታ እና እምነት፣ ለእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ሁሉ በውስጡ “አዎን” ከሌለው፣ እግዚአብሔር በእያንዳንዱ የወደፊት ሁኔታ ውስጥ ቆራጥ ለሆነ አገልግሎት የሚሰጠውን ብርታትና ኃይል እንዳንቀበል ያደርገናል (1ኛ ጴጥሮስ 4፥11)።
በእግዚአብሔር የወደፊት ጸጋ ላይ ያለውን የእምነትን ባህርይ ለመረዳት እንጸልይ። ይህንንም ስንረዳ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ከሚያቀሉብን እና ከሚያድበሰብሱብን መረዳቶች መራቅ እንችላለን። በእርግጥም እጅግ ውድ፣ አስደናቂ እና ጥልቅ ነው።