ለማይቻለው ማመን | ሰኔ 5

ይልቁንም በእምነቱ በመጽናት ለእግዚአብሔር ክብርን ሰጠ እንጂ፣ የእግዚአብሔርን ተስፋ አልተጠራጠረም፤ እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም በሙሉ ልብ ርግጠኛ ነበር። (ሮሜ 4፥​20–21)

እምነት የእግዚአብሔርን የወደፊት ጸጋ እንዴት እንደሚያከብር የሚያስረዳ ልዩ ምክንያት ጳውሎስ ይነግረናል። እግዚአብሔር ለወደፊት የገባውን ቃል ለመፈጸም ታማኝ እንደሆነ፣ በቂ ኃያል እንዳለው እና ጥበብ የተሞላ እንደሆነ በሙሉ ልብ የሚያምን እምነት እግዚአብሔርን የሚያከብር እምነት ነው።

ይህንን እምነት አብርሃም ለእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ከሰጠው ምላሽ ጋር በማነጻጸር ጳውሎስ ያስረዳናል። ምንም እንኳን ቢያረጅም፣ ሚስቱም መካን ብትሆንም፣ የብዙ አሕዛብ አባት እንደሚሆን ግን እግዚአብሔር ቃል ሰጥቶት ነበር (ሮሜ 4፥18)። “ምንም ተስፋ በሌለበት፣ አብርሃም በተስፋ አመነ” ይለናል። ይህም ማለት፣ ሰዋዊ ማስረጃዎቹ በሙሉ አይሆንም የሚሉ በሆኑበት፣ እርሱ ግን ወደፊት በሚመጣው በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ጸጋ ላይ እምነቱን አጸና።  

እርሱ የመቶ ዓመት ሰው ሆኖ ሳለ፣ የራሱም ሰውነት ሆነ የሣራ ማሕፀን ምዉት እንደ ነበረ እያወቀ በእምነቱ አልደከመም። ይልቁንም በእምነቱ በመጽናት ለእግዚአብሔር ክብርን ሰጠ እንጂ፣ የእግዚአብሔርን ተስፋ አልተጠራጠረም፤ እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም በሙሉ ልብ ርግጠኛ ነበር። 

(ሮሜ 4፥​19–21)

የአብርሃም እምነት፣ እግዚአብሔር የብዙ አሕዛብ አባት እንደሚያደርገው በገባው የተስፋ ቃል ላይ የተጣለ እምነት ነበር። ይህም እምነት፣ ትኩረትን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት እና ልዕለ-ተፈጥሯዊ ሃብቱ ላይ በማድረግ፣ እግዚአብሔርን አክብሮታል።  

አብርሃም ልጅን ለመውለድ እጅግ አርጅቶ ነበር። ሳራም መካን ነበረች። ይህም ብቻ አይደለም። እንዴት ነው አንድ ወይም ሁለት ልጅ እንደሚኖረው እያወቀ፣ እግዚአብሔር እንዳለው የ“ብዙ አሕዛብ” አባት መሆን እንደሚችል ያመነው? ይህ ሁሉ ፈጽሞ የማይቻል ይመስል ነበር።

ስለዚህ አብርሃም፣ በእምነት፣ በሰው ልጅ የማይቻለውን እግዚአብሔር ማድረግ እንደሚችል፣ ደግሞም እንደሚያደርገው ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ በመሆን አክብሮታል። እኛም የተጠራነው ተመሳሳይ እምነት እንዲኖረን ነው። ከሁሉም አቅም በላይ የሆነውን፣ ለራሳችንም ፈጽሞ ማድረግ የማንችለውን እግዚአብሔር እንደሚያደርግልን እንድናምን ተጠርተናል።