ይልቁንም በእምነቱ በመጽናት ለእግዚአብሔር ክብርን ሰጠ እንጂ፣ የእግዚአብሔርን ተስፋ አልተጠራጠረም። (ሮሜ 4፥20)
አቤት፤ ቅድስናን እና ፍቅርን ለመያዝ በምናደርገው ሩጫ እግዚአብሔር ከብሮ ምነኛ ደስ ባለን? ነገር ግን ሩጫችን በተስፋ ቃሎቹ ላይ በመታመን ካልተደረገ በቀር እግዚአብሔር አይከበርም።
ስለ ኃጢአታችን በተሰቀለውና ለጽድቃችንም በተነሣው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ራሱን ሙሉ በሙሉ የገለጠልን አምላካችን የሚከብረው የተስፋ ቃሉን በደስታና በጽናት ስንቀበል ነው። ለእነዚህ ተስፋዎች ያወጣው ዋጋ ውድ ነው፣ የልጁን ደም አስከፍለውታል (ሮሜ 4፥25)።
ድካማችንን እና ውድቀታችንን አምነን ራሳችንን በፊቱ ስናዋርድ እና በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ ጸጋን እንደሚሰጠን በእርሱ ስንታመን እግዚአብሔር ይከብራል። በሮሜ 4፥20 ላይ፣ ጳውሎስ ስለ አብርሃም እምነት ሲናገር፣ “ይልቁንም በእምነቱ በመጽናት ለእግዚአብሔር ክብርን ሰጠ እንጂ፣ የእግዚአብሔርን ተስፋ አልተጠራጠረም” ይላል።
በእምነቱ በመበርታት እግዚአብሔርን አከበረ። በእግዚአብሔር ተስፋዎች ላይ የምንጥለው እምነት ጥበቡን፣ ኃይሉን፣ መልካምነቱን እና ታማኝነቱን ስለሚያውጅ አምላካችንን እጅግ ያከብረዋል። ስለዚህም፣ በእግዚአብሔር የጸጋ ተስፋ በመታመን መኖርን ካልተማርን፣ ምንም ያህል ትጉ የኀይማኖት ሥርዓት ፈጻሚዎች ብንሆን እንኳ፣ እግዚአብሔር ግን አይከብርም።
በሚሰጠን ጸጋ ላይ በትሕትና ተደግፈን ለመቀደስ ስንተጋ፣ ያኔ እግዚአብሔር ይከብራል።
የተሃድሶ አባት የሆነው ማርቲን ሉተር እንዲህ ይላል፦ “እምነት የሚታመንበትን አካል እውነተኛ እና እምነት ሊጣልበት የተገባ አድርጎ ስለሚቆጥረው፣ በጥንቃቄና በታላቅ አክብሮት ያከብረዋል።” እውነት ነው፤ ታማኝ ሆኖ የሰጠው ሰጪ ክብርን ይቀበላል።
ለእግዚአብሔር ክብር እንዴት መኖር እንዳለብን እንማር ዘንድ እንመኝ፣ እንጓጓ፣ እንጸለይ። ይህም የሚሆነው እግዚአብሔር በሚሰጠን ጸጋ በእምነት ስንኖር እና አለማመንን ስንዋጋ ነው።