“ስሙ ቀናተኛ የሆነው እግዚአብሔር (ያህዌ) ቀናተኛ አምላክ (ኤሎሂም) ነውና ሌላ አምላክ አታምልክ።” (ዘፀአት 34፥14)
እግዚአብሔር ለስሙ ክብር እጅግ ቀናተኛ ነው። ልባቸው የእርሱ መሆን ሲገባው፣ ከባሏ ሌላ እንደምታይ ሴት ወደ ሌላ በሚመለከቱት ላይ በታላቅ ቁጣ ይገለጣል።
ለምሳሌ በሕዝቅኤል 16፥38-40 እምነት ለሌላቸው እስራኤላውያን እንዲህ ይላል፦
“ለአመንዝራና ለነፍሰ ገዳይ ሴቶች የሚገባውን ፍርድ እፈርድብሻለሁ፤ በመዓቴና በቅናቴ እስከ ደም እበቀልሻለሁ። ለወዳጆችሽ አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ እነርሱም ጒብታሽንና የማምለኪያ ኰረብታሽን ያፈርሳሉ፤ ልብስሽን ይገፉሻል፤ ምርጥ ጌጣጌጥሽን ይቀሙሻል፤ ዕርቃንሽንና ባዶ እጅሽን ያስቀሩሻል። ሕዝብ ያነሣሡብሻል፤ በድንጋይ ይወግሩሻል፤ በሰይፍ ይቈራርጡሻል።”
ይህንን ማስጠንቀቂያ እንድታዳምጡት አሳስባችኋለሁ። እግዚአብሔር ላልተከፋፈለ ፍቅራችሁ እና መሰጠታችሁ ታላቅ ቅንዓት አለው። ፍቅራችሁን ከእግዚአብሔር ሊሰርቅ የመጣ ማንኛውም አታላይ ነገር በኋላ ተመልሶ እርቃናችሁን ያስቀራቹኃል፤ ይቆራርጣችኋል።
በእግዚአብሔር የተሰጣችሁን ሕይወት፣ በእርሱ ላይ ዝሙት ለመፈጸም መጠቀም እጅግ የሚያስፈራ ነገር ነው።
ነገር ግን በእውነት ከክርስቶስ ጋር ለተጣመራችሁት፤ ሁሉንም ክዳችሁ ለእርሱ ለመኖር ቃል ኪዳናችሁን ለምትጠብቁት ለእናንተ የእግዚአብሔር ቅንዓት የሚመች እና ተስፋ የሚሰጥ ነገር ነው።
እግዚአብሔር ለክብሩ እጅግ ቀናተኛ ከመሆኑ የተነሳ በሚታመኑት የእርሱ ሕዝቦች (ታማኝ ሙሽሪት) ላይ የመጣ ነገር ሁሉ በመለኮታዊ ቁጣ የሚመለስ ይሆናል። ይህም በእርሱ ለሚታመኑት የእርሱ ሕዝቦች – ታማኝ ሙሽሪት ለሆኑት – መልካም ዜና ነው።
የእግዚአብሔር ቅንዓት እንደ ጋለሞታ ለሚኖሩት፣ ልባቸውን ለዓለም ለሸጡት እና በአምላክ ላይ ለሚያላግጡት ሁሉ ታላቅ ሥጋት ነው (ያዕቆብ 4፥3-4)። ነገር ግን ቃል ኪዳናቸውን ለሚጠብቁት እና በዚህ ዓለም ላይ እንደ እንግዶች ለሚኖሩት ታላቅ የምቾት ምንጭ ነው።