ደስታን ለማግኘት 15 መንገዶች | ግንቦት 1

የሕይወትን መንገድ ታሳየኛለህ፤ በአንተ ዘንድ የደስታ ሙላት፣ በቀኝህም የዘላለም ፍሥሓ አለ። (መዝሙረ ዳዊት 16፥11)

በዚህ ኅጢአትና ሥቃይ በሞላበት ሕይወት ውስጥ ደስታ እና እምነት በብዙ ትግል የሚገኙ ነገሮች ናቸው። እናም ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል” ይለዋል (1ኛ ጢሞቴዎስ 6፥12)። ደስታም የሚገኘው እንዲሁ በትግል ነው። ለማገኘት ልንተጋና ልንጋደል ይገባል። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች፣ “ደስ እንዲላችሁ ከእናንተ ጋር እንሠራለን” ያላቸው ለዚህ ነው (2ኛ ቆሮንቶስ 1፥24)።

ታዲያ ለደስታ እንዴት እንታገል? ለዛሬ 15 ነጥቦችን እንመልከት፦

  1. እውነተኛ በሆነ ደስታ በእግዚአብሔር መደሰት ስጦታ መሆኑን ተገንዘቡ።
  2. ለደስታ ያለማቋረጥ መታገል እንዳለብን አስቡ። ከዚያ ደግሞ፣ ከመጀመሪያው ነጥብ ጋር የሚጋጭ ነው ብላችሁ ግራ አትጋቡ።
  3. በሕይወታችሁ ውስጥ ያሉትን የምታውቋቸውን ሁሉንም ኃጢአቶች በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በማጥቃት ትጉ።
  4. ልበ-ሙሉ ሆኖ የመጸጸትን ሚስጥር ተረዱ፣ ደግሞም እንደ ጸደቀ ኃጢአተኛ ኀጢአትን እንዴት መታገል እንደሚቻል ተማሩ።
  5. ጦርነቱ በዋነኛነት እግዚአብሔርን አጥርቶ ለማየት የሚደረግ ትግል መሆኑን ተገንዘቡ። ውግያው ለማየት ነው።
  6. የእግዚአብሔርን ቃል በቀንና በሌሊት አሰላስሉ።    
  7. የልቦናችሁ ዓይኖች እንዲከፈቱና እግዚአብሔርን በሙሉ ልባችሁ እንድትፈልጉ ያለማቋረጥ በብርቱ ጸልዩ።
  8. ራሳችሁን ከማዳመጥ ይልቅ ለራሳችሁ መስበክን ተማሩ።
  9. በእግዚአብሔር ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ ተይዘው እግዚአብሔርን እንድትመለከቱ እና መልካሙን ገድል እንድትጋደሉ ከሚረዷችሁ ሰዎች ጋር ጊዜን አሳልፉ።
  10. እግዚአብሔር ያለ በማይመስልባቸው ድቅድቅ ሌሊቶች ታገሡ።
  11. የእግዚአብሔር ስሪት የሆነው ሰውነታችሁ የሚያስፈልገውን ዕረፍት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና ትክክለኛ አመጋገብ ስጡት።
  12. እግዚአብሔር ራሱን በተፈጥሮ ውስጥ መግለጡን በማወቅ በትክክል ተጠቀሙበት። ለምሳሌ፦ ጫካዎችን እና ተራሮችን ጎብኙ፣ በድንቅ አሠራሩ ተገረሙ።
  13. ስለ ታላቁ እግዚአብሔር እና ስለ ቅዱሳን የሕይወት ታሪክ የሚያወሩን ታላላቅ መጻሕፍትን አንብቡ።
  14. ለሌሎች ስትሉ ከባዱንና የተወደደውን ነገር አድርጉ፤ ወንጌልን በንግግራችሁ እና በመልካም ሥራችሁ መሥክሩ።
  15. ለክርስቶስ ወንጌል ዓለም አቀፍ ራዕይ ይኑራችሁ፤ በወንጌል ላልተደረሱት ነገዶች ራሳችሁን አፍስሱ።
ለተጓዳኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት፣ When I Don’t Desire God: How to Fight for Joy የሚለውን መጽሐፍ ይመልከቱ።