እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ። አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ። (ኢሳይያስ 41፥10)
ላይሳኩ ስለሚችሉ አዳዲስ ስራዎች ወይም ስብሰባዎች ስጨነቅ፣ በብዛት ከምጠቀምባቸው የተስፋ ቃሎቼ አንዱ በሆነው በኢሳይያስ 41፥10 አለማመንን እዋጋለሁ።
ለሦስት ዓመታት ወደ ጀርመን ሀገር ለትምህርት በሄድኩበት ቀን፣ አባቴ ከቤት ደውሎልኝ የዚህን ጥቅስ የተስፋ ቃል በስልክ ሰጠኝ። ለሦስት ዓመታት ያህል፣ በሚገርሙ የጭንቀት ጊዜያት ውስጥ እንዲያሳልፈኝ ይህንን ጥቅስ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ጊዜያት ለራሴ መጥቀስ ነበረብኝ።
የአዕምሮዬ ሞተር ቀዝቀዝ ባለ ጊዜ፣ በጭንቅላቴ ትር ትር የሚለው የኢሳይያስ 41፥10 ድምጽ ነው። ይህን ጥቅስ እወደዋለሁ።
በእርግጥ፣ በእምነቴ የጦር ዕቃ ውስጥ ያለው ሰይፍ ይህ ብቻ አይደለም።
አገልግሎቴ ከንቱና ትርጉም የለሽ እንደሆነ አስቤ ስጨነቅ፣ በኢሳይያስ 55፥11 የተስፋ ቃል፣ አለማመንን እዋጋለሁ። ክፍሉ እንደዚህ ይላል፦ “ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ፣ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ ነገር ግን የምሻውን ያከናውናል፤ የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል”።
ሥራዬን ለመሥራት እና በተሳካ ሁኔታ ለመፈጸም በጣም ደካማ እንደሆንኩ አስቤ ስጨነቅ፣ በክርስቶስ የተስፋ ቃል አለማመንን እታገለዋለሁ፣ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” (2ኛ ቆሮንቶስ 12፥9)።
ነገ መወሰን ስላሉብኝ ውሳኔዎች ስጨነቅ፣ “አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ” በሚለው የተስፋ ቃል አለማመንን እዋጋለሁ (መዝሙረ ዳዊት 32፥8)።
ተቃዋሚዎችን ስለ መጋፈጥ ስጨነቅ፥ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፣ ማን ሊቃወመን ይችላል?” በሚለው የተስፋ ቃል አለማመንን እዋጋለሁ (ሮሜ 8፥31)።
ስለምወዳቸው ሰዎች ደኅንነት ስጨነቅ፥ እኔ ክፉ ሆኜ ለልጆቼ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቅሁ፣ “የሰማዩ አባታችሁማ ለሚለምኑት መልካም ስጦታን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም? ” በሚለው የተስፋ ቃል አለማመንን እዋጋለሁ (ማቴዎስ 7፥11)።
ስለዚህም፣ አለማመንን በመጽሐፉ ውስጥ ባሉት የተስፋ ቃሎች ሁሉ ታገሉ። ነገር ግን ለሁሉም ጊዜ የሚሆን አንድ መሰረታዊ የጥቅስ ሰይፍ ቢኖራችሁ ደግሞ ይጠቅማችኋል። ያ ሰይፍ ለእኔ ኢሳያስ 41፥10 ነው። “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ። አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ።” የተወደደ እና እጅግ ውድ የሆነ የተስፋ ቃል!