ፍጹም መጽደቅ | የካቲት 29

እግዚአብሔር የመረጣቸውን የሚከስ ማን ነው? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው። (ሮሜ 8፥33)

ጳውሎስ “እግዚአብሔር የመረጣቸውን የሚከስ ማን ነው?” ብሎ ከጠየቀ በኋላ፣ “ማንም አይከሰንም! ጸድቀናል” ብሎ መመለስ ይችል ነበር። ቢልም ደግሞ እውነት ነው። ነገር ግን እንደዚያ አላለም። “የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው” በማለት ይመልሳል።

አጽንኦት የሰጠው ድርጊቱ ላይ ሳይሆን አድራጊው ላይ ነው።

ለምን? ምክንያቱም የዚህ ቃል መገኛ የሆነውን የዓለምን የፍርድ ቤት አሰራር ብንመለከት፣ አንድ ዳኛ አንድ ተከሳሽ ላይ ጥፋት የለበትም ብሎ ቢወስን፣ ከእርሱ በላይ ሥልጣን ያለው ዳኛ ያንን ውሳኔ ይሽረዋል።

ጥፋተኛ ሆናችሁ፣ ነገር ግን የቀበሌ ዳኛ ነፃ ብሎ ቢለቃችሁ፣ ከፍተኛው አቃቤ ሕግ እናንተን መክሰስ የሚችል ከሆን ምን ይጠቅማችኋል? እሱ ደግሞ ነፃ ናችሁ ቢል እንኳ፣ ንጉሡ የሚከሳችሁ ከሆነ ምን ጥቅም ይኖረዋል?

የዚህ ሁሉ ዋና ሃሳብ ይህ ነው፦ ከእግዚአብሔር በላይ የሆነ ፍርድ ቤት የለም። እግዚአብሔር፣ “ጥፋት የለባችሁም” ካላችሁና በፊቱ ጻድቅ አድርጎ ከቆጠራችሁ ማንም ይግባኝ ሊጠይቅ ወይም ሊቃወማችሁ አይችልም። ማንም የሕግ አተረጓጎም ችግር ወይም የተዛባ ፍርድ አለ ሊል አይችልም። ማንም በእናንተ ላይ ሌላ ክስ ሊያመጣባችሁ አይችልም። የእግዚአብሔር ውሳኔ የበላይ እና የመጨረሻ ነው።

ተመርጣችሁ፣ በኢየሱስ በማመን ከክርስቶስ ጋር አንድ የሆናችሁ ሁሉ ይህን ስሙ፦ ያጸደቃችሁ እግዚአብሔር ራሱ ነው። አንድ ታላቅ ነብይ ወይም ተራ የሰው ዳኛ አይደለም። ከሰማይ የመጣ ሊቀ መልአክም አይደለም። ነገር ግን ያጸደቃችሁ የዓለም ፈጣሪ፣ የሁሉ ነገርም ባለቤት የሆነው፣ ደግሞም አጽናፈ ዓለምን፣ እያንዳንዱ ሞለኪውል እና ሰውን ሁሉ የሚገዛው እግዚአብሔር ነው።

ዋና ሃሳቡ ይሄ ነው፦ በታላቅ መከራ ውስጥ የማይናወጥ ደኅንነት ነው። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ እኛን በመቃወም ማንም ሊሳካለት አይችልም። እግዚአብሔር ልጁን ከሰጠን፣ ለእኛ መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ አብልጦ ይሰጠናል። በእርግጥም ያጸደቀን እግዚአብሔር ከሆነ፣ የትኛውም ክስ በእኛ ላይ ሊጸና አይችልም።