ይልቁንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም ይፈጽም ዘንድ ለሥጋ በዐሳባችሁ አትመቻቹለት። (ሮሜ 13፥14)
እኛ ክርስቲያኖች፣ በውኃ ማዕበል እንደሚነዳ ዓሳ፣ ከዘመኑ ባህል ጋር ዝም ብለን የምንጓዝ አይደለንም። በመንፈሱ ኃይል የምንኖርና መንገዳችንን በእግዚአብሔር ቃል የምንቃኝ ነን። እንደ ዓሳ-ነባሪ በማዕበል ውስጥ እንዋኛለን። ይህንንም የምንተገብርበት አንዱ መንገድ የዘመኑን የዲጅታል ዓለምና አደጋዎቹን በጥንቃቄ በማጤን ነው። ይህንን ለማድረግ የሚረዱንን አምስት ነጥቦች እንመልከት፦
- ሁሉን የማወቅ ጉጉት ወጥመድ
ዲጅታል መሳሪያዎች የማያልቅ የእውቀት እና የምርምር እድልን ይዘው መጥተዋል። መሰረታዊና አስፈላጊ ናቸው የተባሉት አሰራሮች እና ሲስተሞች ሳይቀሩ የረጅም ሰዓት ምርምርና ሙከራን ይጠይቃሉ። በተጨማሪም፣ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሱስ የሚያስይዙ መተግበሪያዎች እና ሶፍትዌሮች በአማላይነታቸው በማጥመድ በርካታ ቀኖቻችሁን ይፈጃሉ።
እነዚህ ሁሉ አታላይ ናቸው። ብዙ ነገር ያሳወቋችሁ እና ፍሬያማ የሆናችሁ አስመስለው ይቀርቡና፣ በቀኑ መጨረሻ ግን በባዶነትና፣ በድብርትና በኪሳራ ስሜት ሞልተዋቸሁ ይሄዳሉ።
ለዚህ መፍትሔው፦ በእነዚህ ዲጅታል ዕቃዎች ላይ የምናሳልፈውን ጊዜ በመገደብ፣ በማይረቡ ተሰጥኦዎች ከመጎበዝ ይልቅ፣ እውነት ላይ እናተኩር።
- ምናባዊው የኢንተርኔት ዓለም ባዶነት
የፈጠራ አቅምና እጅግ ብሩህ አእምሮ ያላቸው በርካታ ሰዎች፣ በጌም እና ሌሎች ከእውነተኛው ዓለም ጋር የማይገናኙን ምናባዊ መዝናኛዎች ውስጥ ከተሞችንና የጦር ሠራዊትን በመፍጠር ጊዜያቸውን ሲያጠፉ ማየት እጅግ ያሳዝናል። ሕይወትን የምንኖረው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። እያንዳንዱ የተሰጠን ችሎታ በእውነተኛው እግዚአብሔር፣ ለእውነተኛው ዓለም የተሰጠን ነው። አጠቃቀማችንም ወደ እውነተኛው መንግስተ ሰማይ፣ አልያም ወደ እውነተኛው ሲኦል ይመራናል። በእውነተኛው እግዚአብሔር ለተጨባጩ ዓለም በተሰጠን ጉልበት የምንሰራው ሥራ ወደ እውነተኛው መንግሥተ ሰማይ ወይም ወደ እውነተኛው ሲኦል የሚመራ ነው። ጊዜ ለማባከን ጊዜ የለም።
ለዚህ መፍትሔው፦ የጉብዝና ዓመቶቻችንን እና የፈጠራ አቅማችንን ለምናባዊ ዓለም ሳይሆን ለእውነተኛው ዓለም እናውለው።
- ከማሽን ጋር “ግላዊ” ግንኙነት
ከየትኛውም ፈጠራ በላይ ኮምፒውተሮች እንደሰው ለመሆን የቀረቡ ናቸው። የተለያዩ ጨዋታዎችን ልትጫወቱባቸው ትችላላችሁ። ያዋሯችኋል። ሁልጊዜም አጠገባችሁ አሉ። ልትተማመኑባቸው ትችላላችሁ። ታዲያ የዚህ ትልቁ አደጋ፣ ከዚህ በቀላሉ ከምናዝዘው ግኡዝ ማሽን ጋር ምቾት እየተሰማን ይመጣና፣ አድካሚ አንዳንድ ጊዜም አሳዛኝ ከሆነው ከእውነተኛ ሰዎች ጋር ከሚደረገው ግንኙነት እየራቅን እንሄዳለን።
ለዚህ መፍትሔው፦ ከእውነተኛ ሰዎች ጋር በሚደረግ ግንኙነት ሊገጥም የሚችልን ችግር በመፍራት፣ ስጋት በሌለው የኤሌክትሮኒክ ግንኙነት እንዳንጠመድ እንጠንቀቅ።
- የፍቅር ግንኙነት አደጋ
የዝሙት ኀጢአት የሚጀምረው በድብቅ ግንኙነት፣ ለብቻ በሚደረግ ረጅም ንግግር፣ እና ባጠቃላይ ነፍስን በማጋራት ነው። ይህንን ደግሞ ማንም ሳያውቅ ማድረግ ደግሞ በዚህ በዲጂታል ዘመን እጅግ ቀላል ሆኗል። “በአካል ተገናኝተን ሌላ ነገር ካልተፈጠረ ምን ችግር አለው?” ብላችሁ ልታስቡ ትችላላችሁ። ችግር አለው።
ለዚህ መፍትሔው፦ ባለትዳር ከሆንን፣ ከትዳር አጋራችን ውጭ ከተቃራኒ ጾታ ጋር የግል ግንኙነትን አንፍጠር። ያላገባን እንደሆነ ደግሞ ከሌላ ሰው የትዳር አጋር ጋር እንዲህ ዓይነት ግንኙነት አይኑረን።
- ፖርኖግራፊ
በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን ፖርኖግራፊ ምስሎች እና ቪዲዮዎች ማግኘት እጅግ ቀላል ሆኗል። ለዝሙት ኀጢአት እንደ ድሮው ሩቅ መሄድ፣ መደባበቅ አይጠበቅባችሁም። ክፍላችሁ ድረስ ሰተት ብሎ ገብቷል። የፖርኖግራፊ ቪዲዮዎችን መመልከት ብቻ ሳይሆን ተሳታፊ መሆንም ተችሏል። ይህንን ድርጊት በአካል ሳትሄዱ የምትፈጽሙበት እድል ተመቻችቶላችኋል።
ፖርኖግራፊ መንፈስን ገዳይ ነው። እግዚአብሔርን ከእኛ ያርቃል። በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ ሴቶችን የስሜት መጠቀሚያ ዕቃ ያደርጋቸዋል። ፀሎትን ያዳክማል። የእግዚአብሔርን ቃል ኢምንት እና ዋጋ ቢስ ያደርጋል። ነፍስን ያረክሳል። የመንፈስን ኀይል ያጠፋል። ትዳር ያፈርሳል። ልጆችን ይበትናል። ሁሉንም ነገር ይበክላል።
ታዲያ ለዚህ መፍትሔው፦ ፍትወትን የሚቀሰቅስ ወሲባዊ ይዘት ያለው ምንም ዐይነት የፖርኖግራፊ ድረገጽን አንክፈት፣ አንመልከት። እግዚአብሔር ደግሞ ይረዳናል።