እግዚአብሔር፣ ለሚወዱትና እንደ ሐሳቡ ለተጠሩት፣ ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲሠራ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን። (ሮሜ 8፥28)
የመከራችንን ጥቃቅን ምክንያቶች አስረግጠን ባናውቃቸውም፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን እምነትን የሚያጸኑ ጉልህ ምክንያቶችን ይሰጠናል።
እነዚህንም የምናስታውስበት መንገድ ቢኖረን መልካም ነው። እነዚህን እውነቶች ዛሬ ላይ ማወቃችን በድንገት መከራ ቢደርስብን ወይም ሌሎችን በመከራቸው የማገዝ እድሉ ቢኖረን፣ ውስጣችን ባዶ እንዳይሆን እና ተስፋ እንዳንቆርጥ ያግዘናል።
እነዚህን አምስት እውነቶች ለማስታወስ በ“R” በሚጀምሩ አምስት ቃላት ላስቀምጥላችሁ። የሚቀላችሁ ከሆነ ሦስቱን ብቻ መርጣችሁ በቃላችሁ ለመያዝ ሞክሩ።
በመከራችን ውስጥ ያሉ የእግዚአብሔር ጉልህ ዓላማዎች እነዚህን ያጠቃልላሉ፦
1. ንሰሓ (Repentance): መከራ፣ ለኛም ሆነ ለሌሎች፣ በምድር ላይ ያለ የትኛውንም ነገር ከእግዚአብሔር አስበልጠን ከመውደድ እንድንመለስ የሚቀርብ ጥሪ ነው።
ሉቃስ 13፥4-5፦ “በሰሊሆም ግንብ ተንዶባቸው የሞቱት ዐሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ በደለኞች ስለ ነበሩ ይመስላችኋል? አይደለም፣ እላችኋለሁ፤ ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ።”
2. መተማመን (Reliance): መከራ ለመኖር የምንጠቀማቸውን የዚህን ዓለም ነገሮች ሳይሆን እግዚአብሔርን እንድንተማመን የሚቀርብ ጥሪ ነው።
2ኛ ቆሮንቶስ 1፥8-9፦ “ወንድሞች ሆይ፤ በእስያ ስለ ደረሰብን መከራ እንድታውቁ እንወድዳለን፤ በሕይወት ለመኖር እንኳ ተስፋ እስከምንቈርጥ ድረስ ከዐቅማችን በላይ የሆነ ጽኑ መከራ ደርሶብን ነበር። በርግጥም የሞት ፍርድ እንደ ተፈረደብን ይሰማን ነበር፤ ይህም የሆነው ሙታንን በሚያስነሣ በእግዚአብሔር እንድንታመን እንጂ፣ በራሳችን እንዳንታመን ነው።”
3. ቅድስና (Righteousness): መከራ በሰማይ ያለው የሚወደን አባታችን ቅጣት ነው፤ ይህም የጽድቁና የቅድስናው ተካፋዮች እንሆን ዘንድ ነው።
ዕብራውያን 12፥6፣ 10-11፦ “… ጌታ የሚወድደውን ይገሥጻል፤ እንደ ልጅ የሚቀበለውንም ይቀጣል። … አባቶቻችን መልካም መስሎ እንደ ታያቸው ለጥቂት ጊዜ ይቀጡን ነበር፤ እግዚአብሔር ግን የቅድስናው ተካፋዮች እንድንሆን ለእኛ ጥቅም ሲል ይቀጣናል። ቅጣት ሁሉ በወቅቱ የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፤ በኋላ ግን ለለመዱት ሰዎች የጽድቅና የሰላም ፍሬ ያስገኝላቸዋል።”
4. ሽልማት (Reward): የዚህ ዘመን መከራችን በሰማይ ታላቅ የሆነን ሽልማትን እየሰራልን ነው፤ ይህም በዚህ ምድር ያጣነውን ሁሉ ነገር በሺሕ እጥፍ የሚክስ ነው።
2ኛ ቆሮንቶስ 4፥17፦ “ምክንያቱም ቀላልና ጊዜያዊ የሆነው መከራችን ወደር የማይገኝለት ዘላለማዊ ክብር ያስገኝልናል።”
5. ማስታወሻ (Reminder): መከራ እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም እንዲሰቃይ በመላክ፣ መከራችንን ለኵነኔ ሳይሆን እኛን ለማነጽ እንዳደረገው ያስታውሰናል።
ፊልጵስዩስ 3፥10፦ “ክርስቶስንና የትንሣኤውን ኀይል እንዳውቅ፣ በሥቃዩ ተካፋይ እንድሆንና በሞቱም እርሱን እንድመስል እመኛለሁ።”
የመከራችንን ጥቃቅን ምክንያቶች ስለማናውቅ፣ የክርስቲያን ልብ በመከራ ውስጥ ስታልፍ “ለምን?” ብላ ማልቀሷን መረዳት ይቻላል – ለምን አሁን፣ ለምን በዚህ መንገድ፣ ለምን ይሄን ሁሉ ጊዜ? ነገር ግን የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ አለማወቃችን፣ እግዚአብሔር በመከራችን ውስጥ ለእኛ ያለውን ጉልህ ዓላማ በቃሉ በመናገር ብርቱ እርዳታ እንደሰጠን እንዲያስረሳን አንፍቀድለት።
“በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ አድርገን እንደምንቈጥር ታውቃላችሁ፤ ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው” (ያዕቆብ 5፥11)።