ሞት ጥቅም የሆነባቸው አምስት ምክንያቶች | ሕዳር 13

ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። (ፊልጵስዩስ 1፥21)

እንዴት ነው መሞት “ጥቅም” የሆነው?

1) መንፈሳችን ፍጹም ይሆናል (ዕብራውያን 12፥22-26)

“እናንተ ግን ወደ ጽዮን ተራራ፣ ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም፣ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ መጥታችኋል፤ በደስታ ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፣ ስማቸው በሰማይ ወደ ተጻፈው ወደ በኵራት ማኅበር ቀርባችኋል፤ የሁሉ ዳኛ ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር፣ ፍጹምነትን ወዳገኙት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፣ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስ፣ እንዲሁም ከአቤል ደም የተሻለ ቃል ወደሚናገረው ወደ ተረጨው ደም ደርሳችኋል።”

ከእንግዲህ ወዲህ ኅጢአት በውስጣችን አይኖርም። ውስጣዊ ጦርነት ያከትማል፤ የወደደንንና ለእኛ ሲል ራሱን አሳልፎ የሰጠውን ጌታ ልብ በሚሰብር ሀዘን ማሳዘን እናበቃለን።  

2) ከዚህ ዓለም ስቃይ እንገላገላለን (ሉቃስ 16፥24-25)

የትንሳኤውን ደስታ ገና ባንቀዳጅም፣ ከህመም በማረፋችን ደስ ይለናል። ኢየሱስ በሞት የሚመጣውን ታላቅ ለውጥ ለማሳየት፣ የአልዓዛርንና የሀብታሙን ሰው ታሪክ ተናግሯል።

“እርሱም፣ ‘አብርሃም አባት ሆይ፤ ራራልኝ፤ በዚህ ነበልባል እየተሠቃየሁ ስለ ሆነ፣ አልዓዛር የጣቱን ጫፍ ውሃ ነክሮ ምላሴን እንዲያቀዘቅዝልኝ እባክህ ላክልኝ’ እያለ ጮኸ። “አብርሃም ግን እንዲህ አለው፤ ‘ልጄ ሆይ፤ አንተ በምድራዊ ሕይወትህ ዘመን መልካም ነገሮችን እንደ ተቀበልህ፣ አልዓዛርም ደግሞ ክፉ ነገሮችን እንደ ተቀበለ አስታውስ፤ አሁን ግን እርሱ እዚህ ሲጽናና፣ አንተ በሥቃይ ላይ ትገኛለህ።”

3) ነፍሳችን ታላቅ ዕረፍትና እፎይታን ታገኛለች (ራዕይ 6፥9-11)

ነፍስን ከሚያሰክን እና እርካታን ከሚሰጥ ከየትኛውም ነገር በላይ ከእግዚአብሔር ዐይን እና እንክብካቤ ሥር መሆን ጥልቅ እርጋታን ይሰጣል።

“አምስተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁትም ምስክርነት የታረዱትን ሰዎች ነፍሶች ከመሠዊያው በታች አየሁ። እነርሱም በታላቅ ድምፅ፣ “ሁሉን የምትገዛ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፤ እስከ መቼ አትፈርድም? እስከ መቼስ ደማችንን በምድር በሚኖሩት ላይ አትበቀልም?” አሉ። ከዚያም ለእያንዳንዳቸው ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፤ ወደ ፊት እንደ እነርሱ የሚገደሉ የአገልጋይ ባልንጀሮቻቸውና ወንድሞቻቸው ቊጥር እስኪሞላ ድረስ ጥቂት ጊዜ እንዲታገሡ ተነገራቸው።”

4) የቤተኝነት ስሜት ይሰማናል (2ኛ ቆሮንቶስ 5፥8)

“አዎን፣ እኛ ደፋር ነን፣ እናም ከሥጋ ርቀን ከጌታ ጋር መሆናችንን እንመርጣለን።”

ባይታወቀውም የሰው ልጅ ሁሉ እግዚአብሔርን ይናፍቃል። ወደ ክርስቶስ ወደ ቤታችን ስንሄድ፣ ከየትኛውም የደህንነት እና የሰላም ስሜት የሚልቅ እርካታ እና ዕረፍት እናገኛለን።

5) ከክርስቶስ ጋር እንሆናለን (ፊልጵስዩስ 1፥21-23)

ክርስቶስ በምድር ላይ ካለ ከማንኛውም ሰው የበለጠ ድንቅ ሰው ነው። አብራችሁ ጊዜ ማሳለፍ ከምትወዷቸው ከማናቸውም በላይ ጥበበኛ ነው፣ ኃያል ነው፣ እናም ደግሞ ደግ ነው። ጌታችን በማይጠገብ መልኩ አስደናቂ ነው። እንግዶቹ መደስት የሚችሉትን ያህል ደስተኛ እንዲሆኑ በእያንዳንዱ ሁኔታ ምን ማድረግ እና ምን ማለት እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል። በፍቅር የተሞላ ነው። የሚወዳቸውን ሰዎች እንደተወደዱ እንዲሰማቸው ለማድረግ ፍቅሩን በማስተዋል መጠቀም ይችልበታል። ስለዚህ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፦ “ለእኔ፣ መኖር ክርስቶስ ነው፤ ሞትም ማትረፍ ነው። በሥጋ ከቈየሁ፣ ፍሬያማ ተግባር ይኖረኛል፤ ነገር ግን የትኛውን እንደምመርጥ አላውቅም። በእነዚህ በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ፣ ከክርስቶስም ጋር ልሆን እናፍቃለሁ፤ ይህ እጅግ የተሻለ ነውና።