“እናንተ አነስተኛ መንጋ የሆናችሁ፤ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ መልካም ፈቃድ ነውና አትፍሩ።” (ሉቃስ 12፥32)
እግዚአብሔር ስለ ገንዘብም ሆነ ስለ ሌሎች የዚህ ዓለም ነገሮች እንዳንሰጋ የሚፈልግበት ምክንያት አለው። ያም ደግሞ ከፍርሃትና ከስጋት ነፃ ስንሆን፣ ስለ እርሱ አምስት ታላላቅ ነገሮችን ስለምናጎላ ነው።
በመጀመሪያ፣ አለመፍራታችን ወይም አለመጨነቃችን የእግዚአብሔርን እረኝነት ምን ያህል እንደምንወደው እና እንደምናከብረው ያሳያል። “እናንተ አነስተኛ መንጋ የሆናችሁ … አትፍሩ” ይለናል። እኛ መንጋዎቹ ነን፤ እርሱም እረኛችን ነው። ታዲያ እረኛችን ከሆነ ደግሞ መዝሙር 23፥1 ለእኛም ይሰራል ማለት ነው፦ “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ አንዳች አይጐድልብኝም።” ይህም ማለት የሚያስፈልገን አንዳች ነገር አይጎድልብንም ማለት ነው።
ሁለተኛ፣ አለመፍራታችን ወይም አለመጨነቃችን የእግዚአብሔርን አባትነት ምን ያህል እንደምንወደው እና እንደምናከብረው ያሳያል። “መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ መልካም ፈቃድ ነውና” ያለን ራሱ ነው። የእርሱ አነስተኛ መንጋ ብቻ አይደለንም፤ ልጆቹም ጭምር ነን፤ እርሱም አባታችን ነው። ያስብላችኋል፤ ደግሞም የሚያስፈልጋችሁን ያውቃል። ይህ ብቻ አይደለም፤ የሚያስፈልጋችሁ ሁሉ እንዲሟላላችሁ ተግቶ ይሰራል።
ሦስተኛ፣ አለመፍራታችን ወይም አለመጨነቃችን የእግዚአብሔርን ንግሥና ምን ያህል እንደምንወደው እና እንደምናከብረው ያሳያል። “እናንተ አነስተኛ መንጋ የሆናችሁ፤ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ መልካም ፈቃድ ነውና አትፍሩ።” “መንግሥቱን” ሊሰጠን የቻለው እርሱ ንጉሥ ስለሆነ ነው። ይህ ደግሞ የሚያስፈልገንን የሚሰጠን አካል ምን ያህል ኃያል እንደሆነ ጨምሮ ያሳያል። “እረኛ” የሚለው ስያሜ ጥበቃንና መግቦትን ያመለክታል። “አባት” የሚለው ደግሞ ፍቅርን፣ ርኅራኄን፣ ሥልጣንን፣ መግቦትንና ምሪትን የሚያመለክት ሲሆን፣ “ንጉሥ” የሚለው ቃል ደግሞ ኃይልን፣ ሉዓላዊነትን እና ስልጣንን ያመለክታል።
አራተኛ፣ አለመፍራታችን ወይም አለመጨነቃችን እግዚአብሔር እንዴት በነጻ የሚሰጥ ለጋስ አምላክ እንደሆነ ያሳያል። አስተውሉ፣ መንግሥቱን ይሰጣችኋል ነው የሚለው። “እናንተ አነስተኛ መንጋ የሆናችሁ፤ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ መልካም ፈቃድ ነውና አትፍሩ።” መንግሥቱን አይሸጥም፣ ግዛቱንም አያከራይም፣ ወይም ለሌላ አያበድርም። እርሱ ወሰን የሌለው ባለጠጋ ነው፤ ክፍያችን አያስፈልገውም። ስለዚህ፣ እግዚአብሔር ሲሰጥ በልግስናና በነፃ ነው። ታዲያማ፣ ሳንፈራ በሚያስፈልገን ነገር ሁሉ ላይ ስናምነው፣ አጉልተን የምናሳየው ይህን ማንነቱን ነው።
በመጨረሻም፣ አለመፍራታችን እና አለመጨነቃችን እግዚአብሔር ይህንን ማድረግ እንደሚፈልግ እንደምናምን ያሳያል። “እናንተ አነስተኛ መንጋ የሆናችሁ፤ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ መልካም ፈቃድ ነውና አትፍሩ።” ይህን ማድረግ ያስደስተዋል። እርሱ ንፉግ አምላክ አይደለም። መንግስቱን ለእኛ መስጠት ደስ ያሰኘዋል። አብዛኞቻችን እንደዚህ ያሉ፣ ከማግኘት ይልቅ መስጠት የሚያስደስታቸው አባቶች የሉንም። ነገር ግን ከእንግዲህ በኋላ በዚህ ልናዝን አይገባንም፤ ምክንያቱም አሁን ላይ ከሁሉም የሚበልጥ አባት፣ እረኛ እና ንጉስ አለን።
ታዲያማ፣ የዚህ ክፍል ዋና ሃሳብ፣ አባታችን እና ንጉሣችን የሆነው እግዚአብሔር መንግሥቱን፣ የዘላለም ሕይወትን፣ ደስታን እና መንግስተ ሰማያትን እንዲሁም እዚያ ለመድረስ የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ ሊሰጠን የሚፈልግ እረኛችን፣ አባታችንና ንጉሣችን በመሆኑ በፍቅር እና በአክብሮት ልንመለከተው ይገባናል የሚል ነው።
እግዚአብሔርን በዚህ መንገድ የምንወደውና የምናከብረው ከሆነ፣ ከፍርሃት እና ከጭንቀት ነፃ እንሆናለን። እግዚአብሔርም ይመለካል።