የለጋስነት አምስት ብድራቶች | የካቲት 30

ችግረኛ ለሆኑ ቅዱሳን ካላችሁ አካፍሉ፤ እንግዶችን ተቀበሉ። (ሮሜ 12፥13)

የእግዚአብሔርን ተስፋዎች ካመንን፣ በለጋስነት ከሰጠንና አንዳችን ለሌላችን ደግሞም ለተቸገሩ ቤታችንን ክፍት ካደረግን ምን ብድራቶችን እናገኛለን?

  1. ቅዱሳን ከመከራቸው እናሳርፋቸዋለን፣ ወይም ቢያንስ እናቀልላቸዋለን፦ “ችግረኛ ለሆኑ ቅዱሳን ካላችሁ አካፍሉ” የሚለው ጥቅስ እየነገረን ያለው ይህንን ነው። ሸክማቸውን እናቀላለን። ጭንቀታቸውን እንቀንሳለን። ተስፋ እንሰጣቸዋለን። ያም ብድራታችን ነው!
  1. የእግዚአብሔርን ክብር እናሳያለን፦ “እንደዚሁም ሰዎች መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰዎች ፊት ይብራ” (ማቴዎስ 5፥16)። በለጋስነት መስጠትና እንግዶችን መቀበል በሕይወታችሁ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔር በጎነት እና ክብር ያንጸባርቃል። እግዚአብሔር ገንዘብና ቤትን የሚሰጠን፣ አጠቃቀማችንን ሰዎች አይተው አማልክቶቻችን እንዳልሆኑ እንዲረዱ ነው። የእኛ አምላክ እግዚአብሔር ነው፣ የከበረ ሀብታችንም እርሱ ነው።
  1. ለእግዚአብሔር ብዙ ምስጋና ይቀርባል፦ “ይህ የምትሰጡት አገልግሎት የቅዱሳንን ጒድለት የሚያሟላ ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር የሚቀርብበት ነው” (2 ቆሮንቶስ 9፥12)። እግዚአብሔር ገንዘብ እና ቤት የሰጠን እኛ እንድናመሰግነው ብቻ ሳይሆን፣ በልግስናችንና በእንግዳ ተቀባይነታችን ብዙዎች ለእግዚአብሔር ምስጋናን እንዲያቀርቡም ጭምር ነው።
  1. ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር እና በውስጣችን ያለው የእርሱ ፍቅር ይረጋገጣል፦ “ማንም ሀብት እያለው፣ ወንድሙ ሲቸገር አይቶ ባይራራለት፣ የእግዚአብሔር ፍቅር እንዴት በእርሱ ይኖራል?” (1 ዮሐንስ 3፥17)። በሌላ አነጋገር፣ በልግስና ስንሰጥ እና ቤታችንን ለሌሎች ክፍት ስናደርግ፣ በሕይወታችን ያለው የእግዚአብሔር ፍቅር ይረጋገጣል። እውነተኛ እንጂ አስመሳይ ክርስቲያኖች አንሆንም።
  1. በመጨረሻም፣ በሰማይ ንብረትን እናከማቻለን፦ “ያላችሁን ሽጡና ለድኾች ስጡ፤ ሌባ በማይሰርቅበት፣ ብል በማይበላበት፣ በማያረጅ ከረጢት የማያልቅ ንብረት በሰማይ አከማቹ፤ ልባችሁ፣ ንብረታችሁ ባለበት ቦታ ይሆናልና” (ሉቃስ 12፥33-34)።

ለጋስነት እና እንግዳ ተቀባይነት በክርስቶስ ውስጥ ላለ ሕይወት ማእከላዊ ናቸው። እንደሚገባን የገንዘብ ቦርሳዎቻችንን እና ቤታችንን አብዝተን የማንከፍተው፣ በፍርሀት እና በስስት ወጥመድ ስለተያዝን ነው። መፍትሔውም፣ የክርስቶስ መገኘት በደስታ ማጣጣም እና የተስፋዎቹን እርግጠኝነት አጥብቆ መያዝ ነው፦ “አምላኬም እንደ ታላቅ ባለጠግነቱ መጠን የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ይሞላባችኋል” (ፊልጵስዩስ 4፥19)።

ብድራታችን የእግዚአብሔር ክብር መታየት፣ የሌሎች ደኅንነት እና በአንድነት ክርስቶስን ለዘላለም የማክበር ደስታ ነው። ስለዚህ እመክራችኋለሁ፦ “ችግረኛ ለሆኑ ቅዱሳን ካላችሁ አካፍሉ፤ እንግዶችን ተቀበሉ።”