በዚያም ወራት ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣች። ቄሬኔዎስ በሶርያ አገር ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያ ጽሕፈት ሆነ። ሁሉም እያንዳንዱ ይጻፍ ዘንድ ወደ ከተማው ሄደ። ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተ ልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ።
የሉቃስ ወንጌል 2፥1-5
እግዚአብሔር መሲሑ በቤተ ልሔም እንዲወለድ አስቀድሞ መወሰኑ ምን ያህል አስደናቂ ነገር እንደሆነ አስባችሁ ታውቃላችሁ (ሚክያስ 5፥2)? ሌላው አስደናቂው ነገር ደግሞ፣ አስቀድሞ የተወሰነው ይህ ብቻ አለመሆኑ ነው። የመሲሑ እናት እና ሕጋዊ አባት ይኖሩ የነበሩት በቤተ ልሔም ሳይሆን በናዝሬት ነበር። የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ እነዚህ ስማቸው ተሰምቶ የማይታወቅ ሁለት ትንንሽ ሰዎች አንድ ነገር ሆነላቸው። ለመጀመሪያው ገና ወደ ቤተ ልሔም ይሄዱ ዘንድ እግዚአብሔር የአውግስጦስ ቄሳርን ልብ አስነሥቶ በሮም ግዛት ሥር ያሉ ሰዎች ሁሉ በየትውልድ ቦታቸው እንዲቆጠሩ አደረገ። ይህ አይገርምም? ሁለት ሰዎች 112 ኪሎ ሜትር እንዲጓዙ ለማድረግ ጠቅላላው ዓለም ላይ ድንጋጌ ወጣ!
ሰባት ቢሊዮን ሰዎች በሚኖሩባት፣ ትልልቅ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች በሚደረጉባት፣ እና ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ትልልቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ባሉባት ዓለም ውስጥ እጅግ በጣም ትንሽ እና ዋጋ ቢስ እንደሆናችሁ ተሰምቷችሁ ያውቃል? እኔ ተሰምቶኝ ያውቃል። በርግጥ ተሰምቷችሁ የሚያውቅ ከሆነ፣ ይህ ስሜት ደስታችሁን ሊወስድ ወይም ልባችሁን ዝቅ ሊያደርግ አይገባም። ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው የፖለቲካ ኅያላን ሆኑ በትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚመሩ ሰዎች ሁሉ፣ ዐውቀውትም ሆነ ሳያውቁት፣ ለራሳቸው ሳይሆን እንደ ማርያም እና ዮሴፍ ላሉ ከናዝሬት ወደ ቤተ ልሔም መሄድ ለተገባቸው ትንንሽ ሰዎች ሲባል፣ እግዚአብሔር እየመራቸው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱሳችን ይነግረናል። እግዚአብሔር ቃሉን ለመፈጸም እና ልጆቹን ለመባረክ ነገሥታትን እና ግዛቶችን በፈቃዱ ይዘውራል።
በራሳችሁ ትንሽ ዓለም ውስጥ በሚገጥማችሁ አስጨናቂ መከራ ምክንያት የጌታ እጅ ያጠረ እንዳይመስላችሁ። እግዚአብሔር ከእኛ በሙሉ ልቡ የሚፈልገው፣ ባለጠጋ ወይም ዝነኛ መሆናችንን ሳይሆን መቀደሳችንን ነው። ያንን ግብ ለመምታት ደግሞ ዓለምን ሁሉ ይገዛል። ምሳሌ 21፥1 በግልጽ ይነግረናል፦ “የንጉሥ ልብ እንደ ውኃ ፈሳሾች በእግዚአብሔር እጅ ነው፤ ወደ ወደደውም ያዘነብለዋል።” እግዚአብሔር የንጉሦችን ልብ ሁልጊዜ የሚያዘነብለው ሕዝቡን ለማዳን፣ ለመቀደስ እና ዘለዓለማዊ ዕቅዱን ለመፈጸም ነው።
እርሱ ለትንንሽ ሰዎች የሚሆን ትልቅ አምላክ ነው። ይህ ታላቅ እውነታ የደስታችን ምክንያት ሊሆን ይገባል። በሰማይ ያለው አባታችን እኛ ልጆቹ የልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን መልክ እንድንመስል እና ወደ ዘለዓለማዊ ክብሩ እንድንገባ፣ በሉዓላዊ ድንጋጌው – ሳይታወቃቸውም ቢሆን – የንጉሦችን፣ የፕሬዘዳንቶችን፣ የጠቅላይ ሚንስትሮችን፣ የገዢዎችን፣ እና መሪዎችን ልብ ሁሉ በፈቃዱ መሠረት እንደፈለገ ያዛል።