ለዘላለም ረክተናል | መጋቢት 25

“የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔም የሚያምን ፈጽሞ አይጠማም (ዮሐንስ 6፥35)።

ይህ ጥቅስ በኢየሱስ ማመን ማለት ከእርሱ ማንነት መብላት እና መጠጣት እንደሆነ ይነግረናል። ነፍሳችን ከእንግዲህ ላይጠማ በኢየሱስ መርካቱን እና መሞላቱን ያበስረናል።

እርካታን ፍለጋ ለምንሮጠው ሩጫ እርሱ የመጨረሻው መልስ ነው። ከእርሱ የተሻለ ወይም የበለጠ የለም።

ዮሐንስ እንድናምነው በሚፈልገው ልክ ኢየሱስን ካመንነው፣ መገኘቱ እና ተስፋው ከየትኛውም የኅጢአት ማታለያ ደስታዎች መብለጣቸውን ከልብ በሆነ መረዳት እንረዳለን (ሮሜ 6፥14)። በኢየሱስ ላይ የሚጣል ይህ ዐይነት እምነት የኅጢአትን ኅይል በመስበር፣ ለቃሉ ታዛዥ መሆን እንድንችል ያደርገናል።

ደግሞም በተመሳሳይ ሁኔታ ዮሐንስ 4፥14 እንዲህ ይላል፦ “እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ግን ከቶ አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት ውሃ ምንጭ ይሆናል።” ከዮሐንስ 6፥35 ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ፣ የሚያድነው እምነት የነፍስን ጥልቅ ጥማት የሚያረካ እንደሆነ ይገልጻል። ይህ እርካታ ሞልቶ እንደሚፈስስ ውሃ የተትረፈረፈ እና ብዙ ፍሬን የሚያፈራ ነው።

ዮሐንስ 7፥37-38ም እንዲህ ይላል፦ “የበዓሉ መጨረሻ በሆነው በታላቁ ቀን፣ ኢየሱስ ቆሞ ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ አለ፤ ‘ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ፤ በእኔ የሚያምን፣ መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውሃ ምንጭ ከውስጡ ይፈልቃል።’”

ክርስቶስ፣ በእምነት አማካይነት፣ ለዘለዓለም የማይቋረጥ የእርካታ ምንጭ፣ የሕይወት ፏፏቴ በመሆን ወደ መንግሥተ ሰማይ ይመራናል። በዚህም ጎዳና ላይ ለብቻችን ጥሎን አይሄድም። ተራ ከሆኑ እርካታዎች እና ከንቱ ኀጢአታዊ የቅዠት ተስፋዎች ነጻ ሊያወጣን መንፈሱን ልኮልናል (ዮሐንስ 7፥38-39)።