ስለ ኢየሱስ ሲባል ይቅርታን ማግኘት | ነሐሴ 28

እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአቴ ታላቅ ነውና፣ ስለ ስምህ ይቅር በልልኝ (መዝሙር 25፥11)።

እግዚአብሔር የአንድ ነገር ትክክለኝነት ለመወሰን ከራሱ በቀር የሚያማክረው ሌላ የበላይ ባለ ሥልጣን የለም። በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ ከሁሉም የሚልቀው የከበረ ነገር የእግዚአብሔር የራሱ ዋጋ ነው። ስለዚህ ለእግዚአብሔር ትክክለኛውን ነገር ማድረግ ማለት ነገሮችን ከራሱ ክብር ጋር በሚስማማ መልኩ ማድረግ ማለት ነው።

የእግዚአብሔር ጽድቅ የሚባለው ከሁሉ በላይ ለሆነው ክብሩ እና ፍጹምነቱ ያለው ቅንዓት፣ ደስታና እርካታ ነው። ለፍጽምናው ካለው ዘላለማዊ ቅንዓት በሚጋጭ መልኩ የሚሰራ ከሆነ ጻድቅ መሆኑ ቀርቶ ጣዖት አምላኪ ይሆናል።

ታዲያ እንደዚህ ያለ ጻድቅ አምላክ እንደ እኛ ያሉ የእርሱን ፍጹምነት ያቃለሉ ኀጢአተኞችን እንዴት ሊወድድ ይችላል? ይህ አይደል የወንጌሉ አስደናቂነት? የድነታችን መሰረት ራሱ የሚገኘው በእግዚአብሔር መለኮታዊ ጽድቅ ውስጥ ነው።

አብ ለልጁ ያለው እጅግ የላቀ ክብር፣ ክፉና ኀጢአተኛ የሆንኩትን እኔን በልጁ በኩል እንድወደድ እና እንደልጁ ተቀባይነት እንዳገኝ አድርጎኛል። ይህም የሆነው የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የእግዚአብሔር ክብር እና ዋጋ በእርግጥም ታላቅ መሆኑን በማሳወጁና በማስመስከሩ ነው።

“እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአቴ ታላቅ ነውና፣ ስለ ስምህ ይቅር በልልኝ” የሚለውን የዘማሪውን ጸሎት ከክርስቶስ የተነሳ በአዲስ መረዳት ልንጸልይ እንችላለን (መዝሙር 25፥11)። በአዲሱ መረዳት ሥር ሆነን፣ “ስለ ስምህ ብለህ በደሌን ይቅር በልልኝ” ከማለት ይልቅ፣ “አምላኬ ሆይ፣ ስለ ኢየሱስ ስም ስትል ኀጢአቴን ይቅር በል” ልንል እንችላለን።

1ኛ ዮሐንስ 2፥12 እንዲህ ይላል፦ “ልጆች ሆይ፤ ኀጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና፣ እጽፍላችኋለሁ።” እየተናገረ ያለው ስለ ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ ኀጢአታችንን በማስተሰረይ የአብን ክብር አረጋገጠ፤ በዚህም “ኀጢአታችን ስለስሙ ሲባል ይቅር ተብሏል።”

እግዚአብሔር ጻድቅ ነው። ኀጢአትን አደባብሶና ሸፍኖ ብቻ አያልፈውም። አንድ ኀጢአተኛ በነጻ ቢለቀቅ፣ በድርጊቱ ያረከሰውን የእግዚአብሔርን ታላቅ ክብር ለመመለስና ከክስ ነጻ ለማውጣት ሌላ ሰው ይሞታል። ክርስቶስም ያደረገው ያንን ነው። ስለዚህም “እግዚአብሔር ሆይ፣ ስለ ስምህ ስትል” እና “ስለ ኢየሱስ ስም ስትል” የሚሉት ልመናዎች አንድ ናቸው። በዚህም ጽኑ የእምነት መልሕቅ ላይ ተማምነን፣ የኀጢአትን ይቅርታ ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር እንጸልያለን።