በቀልህን ለእግዚአብሔር አስረክብ | ሐምሌ 4

“ወዳጆቼ ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ቊጣ ፈንታ ስጡ እንጂ አትበቀሉ፤ “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።” (ሮሜ 12፥19)

ለምሬትና ለበቀል ያለንን ዝንባሌ በማሸነፍ ሂደት ውስጥ ይህ ተስፋ እጅግ ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው? ይህ የሆነበት ምክንያት፣ ለመቆጣታችን ምክንያት ሊሆኑ ከሚችሉ በርካታ ምክንያቶች መካከል ከሞላ ጎደል ተገቢ ከሆነ ስሜት ለሚመነጨው ቁጣ መልስ ስለሚሰጥ ነው።

በርግጥ በብዙ ሁኔታዎች እውነተኛ በደል ደርሶብን ይሆናል። ተበድለናል። ስለዚህም ለደረሰብን ጉዳት ፍትሕ መፈለጋችን ሙሉ በሙሉ ስሕተት አይደለም። ስሕተቱ እኛው ራሳችን ይህን ፍትሕ ማስፈን እንዳለብን ሲሰማንና ፍትሑ እስኪሆን ድረስ በመራራነት ስንሞላ ነው። ይህ ደግሞ ፍፁም ስሕተት ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለሁ፣ እኔ እና ባለቤቴ ኖኤል እርስ በእርስ በደንብ ለመተዋወቅ ግንኙነት ለጀመሩ ጥንዶች በተዘጋጀ ትንሽ ቡድን ውስጥ ነበርን። አንድ ቀን ምሽት ስለ ቁጣ እና ይቅርታ ስንነጋገር ከነበሩት ወጣት ሚስቶች አንዷ በልጅነቷ እናቷ ያደረገችባትን ነገር ይቅር እንደማትላትና ይቅር ልትላትም እንደማትችል ስትናገር አስታውሳለሁ።

ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ ይቅር አለማለትን በተመለከተ በሚሰጣቸው ትእዛዛትና ማስጠንቀቂያዎች ላይ ተነጋገርን።

  • “እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ፣ እናንተም ይቅር ተባባሉ፤ እርስ በርሳችሁ ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ።” (ኤፌሶን 4፥32)
  • “ነገር ግን የሰዎችን ኀጢአት ይቅር የማትሉ ከሆነ፣ አባታችሁም ኀጢአታችሁን ይቅር አይልላችሁም።” (ማቴዎስ 6፥15)

ሆኖም ግን ፍጹም ልትስማማ አልፈለገችም፤ ስለዚህ በእንደዚህ አይነት ምሬትና ይቅር በማይል ልብ የምትቀጥል ከሆነ ነፍሷ ትልቅ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ አስጠነቀቅኳት። ነገር ግን አሁንም መልሳ ይህን ልታደርግ እንደማትችል፣ እናቷንም ይቅር እንደማትል አስረግጣ ነገረችን።

እንደዚህ ያለውን ገዳይ የበቀል እና የመራርነት መንፈስ እንድናሸንፍ የሚረዳን የእግዚአብሔር የፍርድ ጸጋ በሮሜ 12 ላይ ተስፋ ሰጥቷል።

ጳውሎስ እዚህ ጋር እያለ ያለው ግልጽ ነው። በቀል የጌታ ስለሆነ፣ የተበደልናቸው በደሎች ሁሉ በእግዚአብሔር እንደሚታዩ እርግጠኞች በመሆን ጉዳዩን በእጁ መተው እንችላለን ይለናል። በበቀል ጥማታችን እንዳንቀጥል ለማበረታታት፣ “እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ይላል ጌታ” የሚል ተስፋ ሰጥቶናል።

አምላካችን እግዚአብሔር ሂሳቦቻችንን በሙሉ የሚያወራርድ አምላክ መሆኑ፣ ይቅር ከማይል መራራ የበቀል መንፈስ ነፃ የሚያወጣ ተስፋ ይሰጠናል። እንዲያውም እኛ ልናስበው ከምንችለው በላይ፣ ፍትኀዊ በሆነ፣ ምሕረት በፈሰሰበት እና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ያደርገዋል። ኃጢአትን ሁሉ ይቀጣል። ማንም፣ በምንም ነገር አያመልጥም። ንስሓ ገብተው በክርስቶስ ለሚታመኑ ሁሉ ኅጢአታቸውን በመስቀሉ ሲቀጣ፣ ንስሓ ያልገቡትን እና እርሱን የማያውቁትን ደግሞ በሲኦል ይቀጣል። ስለዚህ ራሳችንን ገለል አድርገን እግዚአብሔር ፍጹም ሥራውን እንዲሠራ ቦታ ልንሰጠው ይገባል።