በምስጋና እግዚአብሔርን አክብሩ | ሕዳር 18

ለብዙ ሰዎች እየደረሰ ያለው ጸጋ፣ ለእግዚአብሔር ክብር በምስጋና ላይ ምስጋናን እንዲጨምር ይህ ሁሉ ለእናንተ ጥቅም ሆኖአል። (2ኛ ቆሮንቶስ 4፥15)

እግዚአብሔርን ማመስገን ደስ የሚል ስሜት ነው። ከጸጋው ውለታ የተነሳ ሐሴት የተሞላ የባለዕዳነት ስሜት ይሰማናል። ስለዚህ በምስጋና ውስጥ ያለውን ስሜት ስናስብ፣ ተጠቃሚዎቹ እኛው እንደሆንን እንረዳለን። ነገር ግን ምስጋና በባህሪው ሠጪውን ያከብራል። አመስጋኝ ስንሆን፣ የጎደለንን ነገር እና የእግዚአብሔርን ቸርነት፣ ብሎም የእግዚአብሔርን ሙላት፣ የክብሩን ባለጠግነት እንገነዘባለን።  

“አመሰግናለሁ” ስል፣ ትሁት ሆኜ የምግብ ቤቱን አስተናጋጅ ከፍ እንደማደርገው ሁሉ፣ ለእግዚአብሔር ምስጋና ሲሰማኝ፣ ራሴን ዝቅ አድርጌ እርሱን ከፍ እያደረግሁ ነው። በእርግጥ ልዩነቱ ለእግዚአብሔር ጸጋ ተከፍሎ የማያልቅ ባለዕዳ መሆኔ ነው፤ እርሱ ለእኔ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ደግሞ ነፃ እና በጭራሽ የማይገባኝ ነው።

ዋናው ነገር ግን ምስጋና ሠጪውን ያከብራል። እግዚአብሔርን ያከብራል። እናም በድካሙ ሁሉ የጳውሎስ የመጨረሻው ግብ ይህ ነው። በእርግጥ ድካሙ ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ነው። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻዋ ግብ አይደለችም። እንደገና ስሙት፦ “ለብዙ ሰዎች እየደረሰ ያለው ጸጋ፣ ለእግዚአብሔር ክብር በምስጋና ላይ ምስጋናን እንዲጨምር ይህ ሁሉ ለእናንተ ጥቅም ሆኖአል”። ሁሉም ለእናንተ ጥቅም፤ ለእግዚአብሔር ደግሞ ክብር!

የወንጌል አስደናቂው ነገር፣ ለእግዚአብሔር ክብር ለመስጠት የሚጠበቅብን ምላሽ እጅግ ቀላል፣ አስደሳች እና ተፈጠሯዊ ምላሽ መሆኑ ነው። እግዚአብሔርን የምናከብረው ለተቀበልነው ጸጋ ልባዊ የሆነ ምስጋናን በማቅረብ ነው። ሁሉን በመቸሩ ውስጥ የሚታየው የእግዚአብሔር ክብር እና ከእጁ ስንቀበል የሚታየው የእኛ ትሕትና የተሞላ ደስታ አብረው የሚሄዱ ናቸው። ልባዊ በሆነ ደስታ የሚቀርብ ምስጋና እግዚአብሔርን ያከብራል።  

ስለ ተቀበለው ጸጋ ለእግዚአብሔር ክብርን የሚሰጥ ሕይወት እና በጥልቅ ደስታ ውስጥ የሚኖር ሕይወት ልዩነት የላቸውም። አንድ የሚያደርጋቸው ደግሞ አመስጋኝነት ነው።