በዋጋ ተገዝታችኋልና፤ ስለዚህ በሰውነታችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ። (1ኛ ቆሮንቶስ 6፥20)
“አምልኮ” የሚለው ቃል፣ የእግዚአብሔርን ወሰን የለሽ ክብር ለማሳየት ሆን ተብሎ የሚደረግን የልብ፣ የአሳብንና የሰውነትን ተግባር የሚያመለክት ቃል ነው። የተፈጠርነውም ለዚህ ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጋራ መዘመር ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ኩሽና መወልወል ሊሆን ይችላል።
ስለ አምልኮ በምታስቡበት ጊዜ፣ በቤተ ክርስቲያን አዳራሽ ውስጥ የሚደረግን የጋራ አምልኮ ስርዓት ብቻ አታስቡ። ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ትልቅ ገደብ ነው። እያንዳንዱ የሕይወታችን ክፍል አምልኮ ሊሆን ይገባል።
ለምሳሌ ያህል፣ ቁርስን እና መክሰስን ውሰዱ። 1ኛ ቆሮንቶስ 10፥31፣ “እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ፣ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” ይላል። ከመብላትና ከመጠጣት በላይ እጅግ የተለመደ እና ሁሉም ሰው የሚያደርገው መሠረታዊ የሆነ ነገር የለም። ጳውሎስም ይህንን ወስዶ፣ መብላታችሁንና መጠጣችሁን ሁሉ አምልኮ አድርጉት ይለናል።
ወይም የግብረ ስጋ ግንኙነትን ውሰዱ። ጳውሎስ የዝሙት ተቃራኒ አማራጭ አምልኮ ነው ይላል።
ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚሠራው ኀጢአት ሁሉ ከአካሉ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚፈጽም ግን በገዛ አካሉ ላይ ኀጢአት ይሠራል። ለመሆኑ፣ ሰውነታችሁ በውስጣችሁ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደሆነ አታውቁምን? ይህም መንፈስ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት ነው። እናንተም የራሳችሁ አይደላችሁም፤ በዋጋ ተገዝታችኋልና፤ ስለዚህ በሰውነታችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።
(1ኛ ቆሮንቶስ 6፥18-20)
ይህም ማለት፣ ወሲብን በአግባቡና በቅድስና በመያዝ በሰውነታችሁ አምልኩ ማለት ነው።
የመጨረሻ ምሳሌ። ሞትን ውሰዱ። ሰውነታችን ሞትን መቅመሱ የማይቀር ነው። እንደውም ሰውነታችን በዚህ ምድር ላይ የሚያደርገው የመጨረሻ ተግባሩ ሞት ነው። አካላችን ይሰናበታል። ታዲያ በዚህ የሰውነታችን የመጨረሻ ድርጊት እንዴት ማምለክ እንችላለን? መልሱን በፊልጵስዩስ 1፥20-21 ላይ እናገኘዋለን። ጳውሎስ ክርስቶስ በሰውነቱ ሞት እንዲከብር፣ እንዲመለክ እና ክብር የተገባው መሆኑ እንዲታይ ተስፋ እንዳደረገ ይናገራል። አክሎም፣ “ለእኔ … ሞት ማትረፍ ነው” ይላል። ሞትን እንደ ትርፍ በመቁጠር፣ የክርስቶስን ወሰን የለሽ ክብር በሞታችን እናሳያለን።
ሰውነት አላችሁ። ነገር ግን የእናንተ አይደለም። “በዋጋ ተገዝታችኋልና፤ ስለዚህ በሰውነታችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።”
ሁል ጊዜ በቤተ መቅደስ ውስጥ ናችሁ። ስለዚህ ሁልጊዜ አምልኩ።