“በዚያ ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ ይህም በእናንተ ፈንታ አብን እለምናለሁ ማለቴ አይደለም፤ ስለ ወደዳችሁኝና ከእግዚአብሔርም እንደ መጣሁ ስላመናችሁ አብ ራሱ ይወዳችኋል።” (ዮሐንስ 16፥26-27)
የእግዚአብሔርን ልጅ ከሆነው በላይ አስታራቂ አታድርጉት።
ኢየሱስ “በእናንተ ፈንታ አብን እለምናለሁ ማለቴ አይደለም” ይላል። በሌላ አነጋገር፣ ራሳችሁ ወደ እርሱ መሄድ የማትችሉ ይመስል፣ ራሴን በእናንተና በአብ መካከል አላስገባም ማለቱ ነው። ለምን? “አብ ራሱ ይወዳችኋል።”
ይህ አስገራሚ ነው። እግዚአብሔር እኛን በቀጥታ ወደ መገኘቱ ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልሆነ አምላክ አድርገን እንዳናስብ ኢየሱስ እያስጠነቀቀን ነው። “በቀጥታ” መግባት እንችላለን። ኢየሱስ እያለን ያለው ይህን ነው፦ “ጥያቄዎቻችሁን እኔ ወደ እግዚአብሔር አልወስድላችሁም። ራሳችሁ ቀጥታ ጠይቁ። ይወዳችኋል። ወደ እርሱ እንድትመጡ ይፈልጋል። በቁጣ ወይም ለቁጣ አይፈልጋችሁም።”
ልብ እንበል። ማንም ኃጢአተኛ ሰው በኢየሱስ ደም ካልሆነ በቀር ወደ አብ ዘንድ መግባት በፍጹም አይችልም (ዕብራውያን 10፥19-20)። ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጃችን ነው (ሮሜ 8፥34፤ ዕብራውያን 7፥25)። በአሁኑ ሰዓት በእግዚአብሔር ዘንድ ጠበቃችን ነው (1 ዮሐንስ 2፥1)። በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ሊቀ ካህናታችን ነው (ዕብራውያን 4፥15-16)። ራሱ “በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ብሎ ተናግሯል (ዮሐንስ 1፥6)።
ይህ ሁሉ እውነት ነው። ነገር ግን ኢየሱስ ምልጃውን ከልክ እንዳናሳልፈው እየጠበቀን ነው። “በእናንተ ፈንታ አብን እለምናለሁ ማለቴ አይደለም፤ ስለ ወደዳችሁኝና ከእግዚአብሔርም እንደ መጣሁ ስላመናችሁ አብ ራሱ ይወዳችኋል።” ኢየሱስ አብሮን አለ። የእግዚአብሔር ቁጣ ከእኛ እንደተነሳ ለዓለም ሁሉ የሚያሳይ፣ ዘወትር ያለና የሚኖር ሕያው ምስክር ነው።
ነገር ግን በዚያ ያለው ለእኛ ለመናገር፣ ወይም ከአብ ርቀታችንን ጠብቀን እንድንቆይ ለማድረግ፣ ወይም የአብ ልብ የተቆጠበ ወይም የተከለከለ ነው ለማለት አይደለም። ለዚህም ነው “አብ ራሱ ይወዳችኋል” የሚለን።
ስለዚህ ኑ። በድፍረት ኑ (ዕብራውያን 4፥16)። በናፍቆትና በጉጉት ኑ። ፈገግታውን ጠብቃችሁ ኑ። በፍርሀት እየራዳችሁ ሳይሆን፣ በደስታ እየተንቀጠቀጣችሁ ኑ።
ኢየሱስ እንዲህ ይላችኋል፦ “ወደ እግዚአብሔር የምትሄዱበትን መንገድን ሰርቼላችኋለሁ። አሁን መካከል ላይ ቆሜ መንገድ አልዘጋባችሁም። ስለዚህ ኑ!”