እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ። (መዝሙር 34፥8)
የእግዚአብሔርን ክብር ቀምሼ አላውቅም ለምትሉ ሰዎች ይህንን ማለት እወዳለሁ፦ በትንሹም ቢሆን ቀምሳችሁታል።
ወደ ሰማይ ተመልክታችሁ ታውቃላችሁ? ሰውስ አቅፏችሁ ያውቃል? ከሚሞቅ እሳት አጠገብስ ተቀምጣችሁ ታውቃላችሁ? በአትክልት ስፍራ ተራምዳችሁ፣ በኀይቅ ዳርቻ ላይ ተቀምጣችሁ ወይም ዥዋዥዌስ ላይ ተጫውታችሁ ታውቃላችሁ? የምትወዱትን መጠጥ ሞቃታማ በሆነ ቀን ላይ ጠጥታችሁ ወይም የሚጣፍጥን ምግብ በልታችሁስ ታውቃላችሁ?
በልባችን ያለ እያንዳንዱ ፍላጎት፣ የእምነታችን አልያም ደግሞ ለመንግሥተ ሰማይ ክብር ያለንን የተጣመመ መረዳት ማሳያ ናቸው።
“የእግዚአብሔርን ክብር ቀምሼ አላውቅም” ትላላችሁ። እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በትንሹም ቢሆን ቀምሳችሁታል። አሁንም ሂዱ፣ ወደ ማዕዱም ቅረቡ። ሂዱ ወደ እግዚአብሔር ወደ ራሱ ቅረቡ።
ጥላውን አይታችኋል፤ አሁን ደግሞ ዋናው አካል ተመልከቱ። በሞቃታማው የጨረር ብርሃን ውስጥ ተራምዳችኋል፤ አሁን ደግሞ ከለላ በሆነው በወንጌሉ መነጽር በኩል ወደ ፀሐይዋ ተመልከቱ። የእግዚአብሔርን ክብር የሚያስተጋቡትን ድምጾች በየቦታው ሰምታችኋል፤ አሁን ደግሞ ዋናውን ሙዚቃ እንድትሰሙ ልባችሁን ቃኙ።
ልባችሁ የሚቃኝበት ምርጡ ቦታ ደግሞ የክርስቶስ ኢየሱስ መስቀል ሥር ነው። “እኛም ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ ከአባቱ ዘንድ የመጣውን የአንድያ ልጅን ክብር አየን” (ዮሐንስ 1፥14)።
የእግዚአብሔርን ክብር በሙሉ መገለጥ ማየት ከፈለጋችሁ፣ ኢየሱስን በወጌላቱ ውስጥ ተመልከቱት — በተለይም ደግሞ ወደ መስቀሉ ተመልከቱ። ይህም እውነተኛ የሆነውን የእግዚአብሔርን ክብር በሁሉ ቦታ ታዩ፣ ትሰሙና ትቅምሱ ዘንድ ዓይኖቻችሁን ያበራል፣ እንዲሁም ልባችሁን ይቃኛል።
የተፈጠራችሁት ለዚህ ነው። ጥላዎችን በማየት ዕድሜያችሁን እንዳትጨርሱ እለምናችኋለሁ። እግዚአብሔር የፈጠራችሁ ክብሩን እንድታዩ እና እንድታጣጥሙ ነው። ከምንም በላይ በሙሉ ልባችሁ ይህንን ፈልጉ። ትንሽ ቀምሳችኋል፤ አሁን ግን ወደ ሙሉ ገበታው ቅረቡ።