ስለዚህ እርሱ በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። (1ኛ ጴጥሮስ 5፥6-7)
ስለ ወደፊቱ መጨነቅ እንዴት የትምክህት መገለጫ ሊሆን ይችላል?
የእግዚአብሔር መልስ ይህንን ሊመስል ይችላል፦
የማጽናናችሁ እኔ፣ እኔው ብቻ ነኝ፤ ሟች የሆኑትን ሰዎች፣ እንደ ሣር የሚጠወልጉትን የሰው ልጆች ለምን ትፈራለህ? – ፍርሀታችሁ በእኔ እምነት ማጣታችሁን ያሳያል፤ እናም ምንም እንኳ የራሳችሁ ችሎታ በቂ እንዳልሆነ ብታውቁም፣ ከእኔ ከሚመጣው ጸጋ ይልቅ ተሰባሪውን የራስ መተማመናችሁን መረጣችሁ። ስለዚህ ይህ ፍርሀታችሁ (ምንም ድካም ቢሆንም) ትዕቢታችሁን ያሳያል።
ኢሳይያስ 51፥12
መፍትሔው በራስ ከመተማመን ይልቅ እግዚአብሔር ቃል በገባው በቂ የጸጋ ኅይል ወደ መታመን መመለስ ነው።
በ1ኛ ጴጥሮስ 5፥6-7 ጭንቀት የትምክህት መገለጫ መሆኑን ማየት ትችላላችሁ፤ በጥቅሶቹ መካከል ያለውን ሰዋሰዋዊ ግንኙነት ተመልከቱ፦ “ስለዚህ እርሱ በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤“ ደግሞም “እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።“
ይህ ማለት የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ መጣል፣ ራሳችሁን በእርሱ ፊት ዝቅ የማድረግ መንገድ ነው ማለት ነው። “ቀስ ብላችሁ ብሉ… አፋችሁን ዘግታችሁ በማኘክ“ ወይም “ተጠንቅቃችሁ ንዱ… አይናችሁን መንገዱ ላይ በማድረግ“ ወይም “ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ…. ጭንቀታችሁን በእግዚአብሔር ላይ በመጣል“ እንደማለት ነው!
ስለዚህ ትዕቢት በእግዚአብሔር ላይ የሚያስጨንቀንን እንዳንጥል ይከለክለናል ማለት ነው። ይህም ያልተገባ ጭንቀት የትዕቢት መገለጫ መሆኑን ያሳየናል፤ ምንም ያህል ደካማ ቢመስልም ነው።
ታዲያ ለምንድን ነው የሚያስጨንቀንን በእግዚአብሔር ላይ መጣል የትዕቢት ተቃራኒ የሆነው? ምክንያቱም ትምክህት ያለበት ሰው እንደሚጨነቅ ማመን አይፈልግም፤ ወይም ደግሞ ራሱ ችግሮቹን መፍታት እንደማይችል መቀበል አይፈልግም፤ ችግር ውስጥ እንዳለ ቢያምንም እንኳ፣ መፍትሔው ከእርሱ የበለጠ ዕውቀት እና ጥንካሬ ያለውን አምላክ ማመን እንደሚጠይቅ በፍፁም መቀበል አይችልም።
በሌላ አባባል፣ ትዕቢት የአለማመን አንዱ መገለጫ ነው። አማኝ በሌላ በኩል እርዳታ እንደሚያስፈልገው ይቀበላል፤ ትዕቢተኛ ይህንን አያደርግም። አማኝ በእግዚአብሔር እርዳታ ይተማመናል፤ ትዕቢተኛ ግን እንዲህ አያደርግም። አማኝ የሚያስጨንቀውን በእግዚአብሔር ላይ ይጥላል፤ ትዕቢተኛ ግን እንዲህ አይደለም።
ስለዚህ የአለማመንን ትዕቢት የምንዋጋበት መንገድ ጭንቀቶቻችንን መቀበል እና “ስለ እኔ ግድ ይለዋል“ በሚለው የጸጋ ቃል እየተመራን ፍርሀቶቻችንን ሁሉ ጠንካራ በሆኑት ትከሻዎቹ ላይ በመጣል ነው።