ነገር ግን ገና ኀጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞተ፤ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያሳያል። (ሮሜ 5፥8)
“ያሳያል” የሚለው ቃል አሁናዊ መሆኑን፣ “ሞተ” የሚለው ቃል ደግሞ ያለፈ መሆኑን ተመልከቱ። “ነገር ግን ገና ኀጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞተ፤ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያሳያል።”
“ያሳያል” የሚለው ቃል፣ ይህ ተግባር አሁንም እየተካሄደ እንዳለ፣ ወደፊትም የሚቀጥል መሆኑን ያመለክታል።
“ሞተ“ የሚለው ቃል ደግሞ የክርስቶስ ሞት አንድ ጊዜ ብቻ የተፈፀመ እና የማይደገም መሆኑን ያሳየናል። “እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቷልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ” (1ኛ ጴጥሮስ 3:18)።
ጳውሎስ “እግዚአብሔር ያሳያል” የሚለውን አሁናዊ ቃል ለምን ተጠቀመ? እኔ የምጠብቀው እንዲህ ይላል ብዬ ነበር፦ “ነገር ግን ገና ኀጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞተ፤ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል” እንዲል ነበር የጠበቅሁት። የክርስቶስ መሞት የእግዚአብሔር ፍቅር ማሳያ አልነበረምን? ታዲያ ይህስ ደግሞ ያለፈ ክስተት አይደለም?
ይህን ጥያቄ ለመመለስ ፍንጭን የምናገኘው፣ ክፍሉን ከፍ ብለን ስናነበው ነው። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን። ትዕግሥት ጽናትን፣ ጽናት የተፈተነ ባሕርይን፣ የተፈተነ ባሕርይ ተስፋን፤ ይህም ተስፋ ለዕፍረት አይዳርገንም” (ሮሜ 5:3-5)።
በሌላ አነጋገር፣ እግዚአብሔር በየትኛውንም መንገድ ውስጥ የሚያሳልፈን ተስፋ ይኖረን ዘንድ ነው። በምናልፍበት ፈተና እና መከራ ሁሉ ውስጥ የማይናወጥ ተስፋ እንዲኖረን እግዚአብሔር ይፈልጋል።
ይህንን ታዲያ እንዴት ማድረግ እንችላለን?
ጳውሎስ ይህንን በቀጣዩ መስመር ላይ ይመልሰዋል፦ “እግዚአብሔር በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ ፍቅሩን በልባችን አፍስሷልና” (ሮሜ 5:5)። የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ፈስሷል። ይህ ሀረግ የሚያሳየን ድርጊቱ በመለወጥ(conversion) ጊዜ የተፈፀመ እውነት መሆኑን፣ ደግሞም አሁንም ያለና የሚሰራ መሆኑን ነው።
እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር፣ አንድያ ልጁን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲሞት አሳልፎ በመስጠት ገልጦታል (ሮሜ 5:8)። ነገር ግን ትዕግስት እና ተስፋ እንዲኖረን ከተፈለገ፣ ይህን የተገለጠውን ፍቅሩን ዛሬም ነገም ልንለማመደው እንደሚገባ ያውቃል።
ስለዚህ፣ ፍቅሩን በመስቀሉ ላይ ብቻ በመግለጥ አያበቃም። ዛሬም በመንፈሱ በልባችን ይገልጥልናል። ይህንንም የሚያደርገው የመስቀሉን ክብር እና መስቀሉ የሚሰጠንን ማረጋገጫ — ማለትም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ማንም ሊለየን እንደማይችል — እንድናይ ደግሞም ይህንን ፍቅር እንድንቀምስ የልቦና ዓይኖቻችንን በማብራት ነው (ሮሜ 8:38-39)።