እግዚአብሔር ይቅር እያለም ፍትሐዊ ነው | ነሐሴ 14

ዳዊት ከፈጸመው የዝሙትና የግድያ ኀጢአት በኋላ፣ ነቢዩ ናታን ወደ እርሱ መጥቶ እንዲህ አለው፣ “እግዚአብሔር ኀጢአትህን አስወግዶልሃል። አንተ አትሞትም፤ ይህን በመፈጸምህ ግን፣ የእግዚአብሔር ጠላቶች እጅግ እንዲያቃልሉት ስላደረግህ፣ የተወለደልህ ልጅ ይሞታል” (2ኛ ሳሙኤል 12፥13-14)።

ይህ ሁሉ እጅግ የሚያስቆጣ ነገር ነው። ኦርዮ ሞቷል። ቤርሳቤህ ተደፍራለች። ሕፃኑም መሞቱ አይቀሬ ነው። ይህ ሁሉ ተከስቶ ሳለ ናታን ግን “እግዚአብሔር ኀጢአትህን አስወግዶልሃል” ሲለው እናነብባለን።

በቃ? እንዲሁ በዋዛ? ዳዊት አመንዝሯል። ሰው እንዲገደል ትእዛዝ ሰጥቷል። ዋሽቷል። “የእግዚአብሔርን ቃል አቃሏል” (2ኛ ሳሙኤል 12፥9)። እግዚአብሔርንም ንቋል። ጌታ ግን እንዲሁ በቀላሉ “ኀጢአቱን አስወገደለት”?!

ታዲያ እግዚአብሔር ምን አይነት ጻድቅ ዳኛ ነው? መድፈር፣ ነፍስ ማጥፋት እና መዋሸትን እንዲሁ በቀላሉ እንዴት ያልፋል? መቼም ጻድቅ ዳኞች ይህንን አያደርጉም።

ዛሬ ላይ ያሉ ሰዎች ከሚቸገሩበት በተለየ መልኩ ጳውሎስ የገጠመው ታላቅ ነገረ-መለኮታዊ አጣብቂኝ ይህ ነበር፤ እግዚአብሔር “ኀጢአትን ይቅር እያለ እንዴት ጻድቅ ሊሆን ይችላል? የዚህን ጥያቄ ደግሞ መልስ በሮሜ 3፥25-26 እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፦

በደሙም በሆነው እምነት፣ እግዚአብሔር የማስተስረያ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦታል፤ ይህንም ያደረገው ቀድሞ የተፈጸመውን ኀጢአት ሳይቀጣ በትዕግሥት በማለፍ ጽድቁን ለማሳየት ነው፤ በአሁኑ ዘመን ይህን ያደረገው፣ ጽድቁን ይኸውም እርሱ ራሱ ጻድቅ ሆኖ፣ በኢየሱስ የሚያምነውን የሚያጸድቅ መሆኑን፣ ለማሳየት ነው።

በሌላ አነጋገር፣ እግዚአብሔር የዳዊትን ኀጢአት ሳይቀጣ እንዲሁ ሸፍኖ እና አድበስበሶ አልፎ ቢሆን ኖሮ፣ በእርግጥም እግዚአብሔር ኀጢአትን ባለመቅጣቱ የሚሰማን ቁጣ ትክክል ይሆን ነበር። ሆኖም ግን እንደዛ አላደረገም።

እግዚአብሔር ከዳዊት ዘመን ጀምሮ ወደፊት በዳዊት ምትክ እስከ ሚሞተው ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ድረስ ያሉትን ዘመናት ይመለከታል፤ ስለዚህም በእግዚአብሔር ምሕረት እና በእግዚአብሔር የወደፊት የማዳን ሥራ ላይ ያለው የዳዊት እምነት ዳዊትን ከክርስቶስ ጋር አንድ ያደርገዋል። በእግዚአብሔር ሁሉን-ዐዋቂነት ውስጥ የዳዊት ኀጢአት በክርስቶስ ላይ ተቆጥሮ፣ የክርስቶስ ጽድቅ ደግሞ የዳዊት ጽድቅ እንደሆነ ተደርጎ በመቆጠሩ፣ እግዚአብሔር በፍትሐዊነት የዳዊትን በደል ስለ ክርስቶስ ሲል ይቅር ብሎ ያልፈዋል ማለት ነው።

ከእግዚአብሔር ልጅ ሞት የሚበልጥ ክፍያ የለም። በእርሱም ሞት ውስጥ የተገለጠው የእግዚአብሔር ክብርና ፍትሕ ታላቅነት እጅግ ገናና እና አስፈሪ ነው። ከዚህም የተነሳ እግዚአብሔር የዳዊትን ዝሙት፣ ነፍስ ማጥፋት እና ውሸት ሳይቀጣ በማለፉ ማንም ተጠያቂ ሊያደርገው አይችልም። ለዳዊት የሚገባው ቅጣት በክርስቶስ ላይ ተጭኖ በእርሱ ምትክ ቅጣቱን ተቀበለ። የእኛንም እንዲሁ። በዚህም የእግዚአብሔር ፍትሐዊነት ጸንቶ ታይቷል።

ስለዚህም፣ እግዚአብሔር ፍጹም የሆነውን ጽድቁን እና ፍትሑን ያስቀጥላል፤ በተመሳሳይም ደግሞ ምንም ያህል ኀጢአታቸው አጸያፊ ቢሆንም በኢየሱስ ላይ እምነት ለጣሉ ሰዎች ምሕረቱን አትረፍርፎ ያሳያል። ይህም እጅግ አስደናቂ የምሥራች ነው።