እግዚአብሔር በትሕትና ውስጥ ይፈውሳል | ጥቅምት 8

መንገዶቹን አይቻለሁ፤ ቢሆንም እፈውሰዋለሁ፤ እመራዋለሁ፤ ለእርሱና ስለ እርሱ ለሚያለቅሱትም መጽናናትን እመልሳለሁ፤ በእስራኤል አልቃሾች ከንፈር ላይ ምሥጋና እፈጥራለሁ። በቅርብና በሩቅ ላሉት ሰላም፣ ሰላም ይሁን፤ እኔ እፈውሳቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር። (ኢሳይያስ 57፥18-19)

የሰው ልጅ ዐመፅ እጅግ የከበደ ቢሆንም እግዚአብሔር ይፈውሳል። እንዴት ነው የሚፈውሰው? እግዚአብሔር በተጨቆኑት እና በትሑታን ውስጥ ይኖራል ይላል (ኢሳይያስ 57፥15)። ነገር ግን በኢሳይያስ 57፥17 ላይ ያሉት ሰዎች ትሑት አይደሉም። የራሳቸውን የትዕቢት መንገድ እየተከተሉ ነው። ታዲያ ፈውሱ ምን ሊሆን ይችላል?

መልሱ አንድ ብቻ ነው። እግዚአብሔር የሚፈውሳቸው በማዋረድ ነው። ትዕቢቱን በማፍረስ ታማሚውን ይፈውሳል። ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት የሚኖራቸው ዝቅ ያሉ ትሑታን ብቻ እስከሆኑ ድረስ (ኢሳይያስ 57፥15)፤ የእስራኤልም ደዌ ትዕቢት እና ዐመፅ ስለሆነ (ኢሳይያስ 57፥17)፤ እግዚአብሔር ደግሞ ሊፈውሳቸው ቃል ከገባ፣ ፈውሱ ትሑት ማድረግ፣ መድኅኒቱም መንፈሳቸውን መስበር ነው ማለት ነው (ኢሳይያስ 57፥18)።

ኤርሚያስ አዲስ ቃል ኪዳን እና አዲስ ልብ ያለውን ኢሳይያስ ሲተነብይ ይህን ይመስላል። እንዲህ ብሏል፦

“”ከእስራኤል ቤትና፣ ከይሁዳ ቤት ጋር” ይላል እግዚአብሔር፤ “አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት፣ ጊዜ ይመጣል … “ነገር ግን ከዚያ ጊዜ በኋላ፣ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው” ይላል እግዚአብሔር፦ “ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ። እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ””(ኤርምያስ 31፥31፣ 33)።

ኢሳይያስም ኤርምያስም ያዩት የታመሙ፣ የማይታዘዙ፣ ልባቸው የደነደነ ሰዎች በመለኮታዊ መንገድ የሚቀየሩበትን ዘመን ነው። ኢሳይያስ ስለፈውስ ሲናገር፤ ኤርምያስ ደግሞ አዲስ ህግ በልባቸው ላይ ስለ መፃፉ አትቷል። ሕዝቅኤል ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፤ አዲስ መንፈስም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፤ የድንጋይ ልባችሁን ከእናንተ አስወግዳለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ” (ሕዝቅኤል 36፥26)።

ስለዚህ በኢሳይያስ 57፥18 ላይ ያለው ፈውስ ትልቅ የልብ ቀዶ ጥገና ነው ማለት ነው። የደነደነ፣ ትዕቢት የተጠናወተው፣ የድንጋይ ልብ ወጥቶ አዲስ ለስላሳ ልብ ይተከላል፤ ይህም ልብ በቀላሉ ትሑት የሚሆን እና ኅጢአት ምቾት የሚነሣው ልብ ነው።

ስሙ ቅዱስ የሆነ፣ ከፍ ያለው እግዚአብሔር፣ ለዘላለም የሚኖረው በዚህ ልብ ውስጥ ነው።