እግዚአብሔር ጣዖት አምላኪ አይደለም | ነሐሴ 23

…በቅዱሳኑ ዘንድ ሊከብርና በሚያምኑበትም ሁሉ ዘንድ ሊገረም በሚመጣበት በዚያን ቀን ይሆናል፤ እናንተም ከሚያምኑት መካከል ናችሁ፤ ምስክርነታችንን ተቀብላችኋልና (2ኛ ተሰሎቄ 1፥10)

በዚህ ክፍል ላይ ጳውሎስ የሚነግረን፣ ክርስቶስ የሚመጣው በቅዱሳኑ ፊት ሊከብር እና ይገረሙበት ዘንድ እንደሆነ ነው። በእርግጠኝነት ለዚህ ዓላማ ነው የሚመጣው ይለናል።

“እግዚአብሔር የራሱን ክብር ከፍ ያደርጋል፤ በሕዝቡም ሊመሰገን ይፈልጋል” ሲባል፣ ሰዎች ይሰናከላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደዚያ እንዳንሆን ስለሚያስተምረን፣ እግዚአብሔር እንዲህ መሆኑ ግር ይላቸዋል። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር “የራሱንም አይፈልግም” ይላል (1ኛ ቆሮንቶስ 13፥5)።

እግዚአብሔር አፍቃሪ ሆኖ ሳለ እንዴት ነው በዚያው መጠን ደግሞ “የራሱን” ክብር፣ ውዳሴ እና ደስታ የሚፈልገው? እግዚአብሔር ሙሉ ለሙሉ ለራሱ ክብር የሚተጋ ከሆነ፣ እንዴት ብሎ ነው ለእኛ መቆም የሚችለው? የሚሉ ጥያቄዎች ይፈጠራሉ።

መልሳችን ይህ ነው፦ እግዚአብሔር ፍጹም፣ ክቡር እና ሙሉ ለሙሉ በራሱ ብቁ በመሆኑ ልዩ ስለሆነ፣ ለእኛ እንዲቆም ካስፈለገ ለራሱ ክብር መቆም አለበት። ለፍጥረት የሚሠራው የትሕትናና ዝቅ የማለት ሕግ በተመሳሳይ መልኩ ለፈጣሪው አይሠራም።

እግዚአብሔር የዘላለም የደስታ ምንጭ ከሆነው ከራሱ ዘወር ካለ፣ አምላክነቱ ያበቃል ማለት ነው። ዘላለማዊ የሆነውን የራሱን ክብር ዋጋ ይክዳል። ከእርሱ ውጪ ሌላ የከበረ ዋጋ ያለው አካል እንዳለ ያመላክታል። ጣዖት አምላኪም ይሆናል።

ይህ ለእኛ ምንም አይጠቅመንም። አምላካችን ጻድቅ ከመሆን ቢጎድል ወዴት እንሄዳለን? የእግዚአብሔር ልብ ከሁሉ የላቀውን ማንነቱን በላቀ ሁኔታ ማክበር ቢያቆም፣ የጸና የእውነት አለት ከየት ልናገኝ እንችላለን? እግዚአብሔር የራሱን ዘላለማዊ ክብር እና ውበት ችላ ካለ፣ ውዳሴያችን ለማን ይሆናል? አድናቆታችንንስ ማን ላይ እናደርጋለን?   

በፍጹም፤ እግዚአብሔር እግዚአብሔርነቱን ለማስተው በመሞከር ለራሱ ያለውን ክብር ወደ ፍቅር አንለውጠውም።

ይልቁንም፣ እግዚአብሔር ፍቅር የሆነበት ዋነኛ ምክንያት፣ ያለ ማቋረጥ የስሙን ምስጋና በሕዝቡ ልብ ውስጥ ስለሚፈልግ እንደሆነ ልንረዳ ይገባል። ሕዝቡ እንዲያከብረው መፈለጉና መፍቀዱ የታላቅ ፍቅሩ ውጤት ነው። በዚህም፤ ለታላቅነቱ የምናቀርበው ምስጋና የደስታችን ፍጻሜና የታላቅነቱም ማሳያ ነው።