“እግዚአብሔር የሕዝቦችን ምክክር ከንቱ ያደርጋል፤ የሕዝብንም ዕቅድ ያጨናግፋል። የእግዚአብሔር ሐሳብ ግን ለዘላለም ይጸናል፤ የልቡም ሐሳብ ለትውልድ ሁሉ ነው።” (መዝሙር 33፥10-11)
“አምላካችንስ በሰማይ ነው፤ እርሱ ደስ የሚለውን ያደርጋል” (መዝሙር 115፥3)። የዚህ ጥቅስ ዋና ሐሳብ እግዚአብሔር የሚያስደስተውን ለማድረግ መብት እና ኅይል እንዳለው መናገር ነው። እግዚአብሔር ሉዓላዊ ነው ማለት ይህ ነው።
ለትንሽ ጊዜ አስቡበት፤ እግዚአብሔር ሉዓላዊ ከሆነና የሚያስደስተውን ካደረገ፣ ሐሳቦቹ ሊጨነግፉ አይችሉም ማለት ነው። “እግዚአብሔር የሕዝቦችን ምክክር ከንቱ ያደርጋል፤ የሕዝብንም ዕቅድ ያጨናግፋል። የእግዚአብሔር ሐሳብ ግን ለዘላለም ይጸናል፤ የልቡም ሐሳብ ለትውልድ ሁሉ ነው” (መዝሙር 33፥10-11)።
እናም የእግዚአብሔር ሐሳቦች የማይጨነግፉ ከሆነ፣ እርሱ ፍጹም ደስተኛ ነው ማለት ነው።
ሁሉም ክርስቲያን ከዚህ ዘላለማዊ እና መለኮታዊ ደስታ ተካፋይ ነው፤ እንዲሁም የበለጠ መካፈል ይመኛል።
መላ ዓለምን የሚመራው እግዚአብሔር ደስተኛ ባይሆን አስባችሁታል? እግዚአብሔር የሚያጉረመርም፣ አኩራፊ እና ድብርት ያለበት ቢሆንስ ኖሮ? እግዚአብሔር በቀላሉ ተስፋ የሚቆርጥ እና ግድ የለሽ ቢሆን ኖሮስ? ከዳዊት ጋር “እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤ አንተን ከልብ እሻለሁ፤ ውሃ በሌለበት፣ በደረቅና በተራቈተ ምድር፣ ነፍሴ አንተን ተጠማች፤ ሥጋዬም አንተን ናፈቀች” ማለት እንችል ነበር? አይመስለኝም (መዝሙር 63፥1)።
ሁላችንም የሚያጉረመርም፣ አኩራፊ እና ድብርት የሚያጠቃቸው አባት እንዳላቸው ልጆች፣ ከእግዚአብሔርም ጋር ግንኙነታችን እንደዚህ ይሆን ነበር። እነዚህ ልጆች አባታቸውን ላለመረበሽ ይጥራሉ፤ ወይም ትንሽ ነገር ሰርተውለት ሊያስደስቱት ይጥራሉ።
ነገር ግን እግዚአብሔር እንዲህ አይደለም። ምንጊዜም አይደክምም ወይም ተስፋ አይቆርጥም። እናም መዝሙር 147፥11 እንደሚለው፣ “እግዚአብሔር… በምሕረቱ በሚታመኑትም ይደሰታል።” ስለዚህ የክርስቲያን ዓላማ ከእግዚአብሔር መሸሽ ወይም መደበቅ ሳይሆን፣ በማይሰበር ፍቅሩ ተስፋ ማድረግ ነው፤ ወደ እርሱ መሮጥ ነው፤ በእግዚአብሔር አብሮነት እና መውደድ መደሰት ነው።