“ዘላለማዊ አምላክ (ኤሎሂም) መኖርያህ ነው፤ የዘላለም ክንዶቹም ከሥርህ ናቸው።” (ዘዳግም 33፥27)
በዚህ ወቅት ኢየሱስ እና ሕዝቡን ለማገልገል በሚያዘጋጁዋችሁ ከባባድ ፈተናዎች ውስጥ እያለፋችሁ ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው እጅግ ሲዋረድ እና አቅመ ቢስነት ሲሰማው፣ ያበቃለት ሊመስለው ይችላል።
ቤተሰባችን በቁርስ ሰዓት ላይ የሚያነበውን ጣፋጭ ጥቅስ አስታውሳለሁ፦ “እግዚአብሔር በከፍታ ስፍራ ላይ ያለ ቢሆንም፣ ዝቅ ያለውን ይመለከተዋል” (መዝሙር 138፥6)።
ከመውረዳችሁ እና ከሥቃያችሁ ብዛት የተነሣ እግዚአብሔር የማያያችሁ እና ግድ የማይለው ቦታ ላይ ደርሳችኋል ማለት አይደለም። እንዲያውም ስትወድቁ ሊይዛችሁ ከታች እየጠበቃችሁ ነው። ሙሴ እንደተናገረው፣ “ዘላለማዊ አምላክ (ኤሎሂም) መኖርያህ ነው፤ የዘላለም ክንዶቹም ከሥርህ ናቸው“ (ዘዳግም 33፥27)።
ስትሸበሩ እና መንሸራተት ስትጀምሩ ይመለከታል፤ ከመውደቃችሁም በፊት ወዲያው ያነሣችኋል። አሁን ግን ሊያስተምራችሁ የፈለገው አዲስ ነገር ይኖራል።
መዝሙረኛው በመዝሙር 119፥71 “ሥርዐትህን እማር ዘንድ፣ በመከራ ውስጥ ማለፌ መልካም ሆነልኝ“ ብሏል። ቀላል ነበር ወይም ደስ የሚል ነበር አላለም፤ ይልቁንም እንዲሁ “መልካም ሆነልኝ“ አለ።
ባለፈው ሳምንት ጄምስ ስቱዋርት በተባለ አንድ ስኮትላንዳዊ ሰባኪ የተፃፈ መጽሐፍ እያነበብኩ ነበር። “በፍቅር አገልግሎት ውስጥ ማገልገል የሚችሉት የተጎዱ ወታደሮች ብቻ ናቸው“ አለ። ለዚህ ነው አንዳንዶቻችሁ ልዩ ለሆነ የፍቅር አገልግሎት እየተዘጋጃችሁ እንደሆነ የማምነው፤ ምክንያቱም እየተጎዳችሁ ስለሆነ ነው።
ችግሮቻችሁ እና ሥቃያችሁ ከእግዚአብሔር ሉዓላዊ ዕቅድ ውጪ የሆኑ እንዳይመስላችሁ። “እኔ ራሴ እርሱ እንደሆንሁ እዩ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እገድላለሁ፤ አድናለሁም“ ያለውን አስታውሱ (ዘዳግም 32፥39)። ከባድ መከራ ውስጥ ላላችሁ ሁሉ እግዚአብሔር ልዩ ጸጋውን ይስጣችሁ፤ አሁንም እያሳያችሁ ያለውን አዲስ እና ልዩ ፍቅር አጥብቃችሁ ፈልጉ።