መልካም ሲያደርግልን እጅግ ደስ ይለዋል | መጋቢት 4

“መልካምን ነገር ለእነርሱ ከማድረግ እንዳልቈጠብና ከእኔም ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በውስጣቸው ላኖር ከእነርሱ ጋር የዘላለም ቃል ኪዳን እገባለሁ። ለእነርሱ መልካም በማድረግ ደስ ይለኛል፤ በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ በእውነት በዚህች ምድር እተክላቸዋለሁ።” (ኤርምያስ 32፥40-41)

ይህ የተስፋ ቃል፣ ብዙ ጊዜ ተስፋ መቁረጥ ሲሰማኝ ከማሰላስላቸው የእግዚአብሔር ተስፋዎች መካከል አንዱ ነው። እግዚአብሔር መልካም ሲያደርግላችሁ እጅግ ደስ ይለዋል ከሚለው በላይ የሚያበረታታ እውነት የት ይገኛል? መልካም ያደርጋል ብቻ አይደለም፤ ግድ ይለዋል ብቻም አይደለም (ይህ በራሱ የከበረ ቢሆንም)፤ ነገር ግን “እጅግ ደስ ይለዋል።“

ሮሜ 8፥28 ላይ “ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲሠራ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን” የሚለውን የተስፋ ቃል ሲፈጽም ግዴታ ሆኖበት አይደለም፤ እጅግ ደስ እያለው ነው። ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ብቻ አይደለም፤ ሁልጊዜም! “መልካምን ነገር ለእነርሱ ከማድረግ እንዳልቈጠብ…” ይላል። ለሚታመኑበት ልጆቹ መልካምን ከማድረግ አይቦዝንም፤ ክንዱም አይዝልም።

ይህ አስደናቂ እውነት እጅግ ሊያስደስተን ይገባል!

ይሄ ግን ሁሌም የሚቻል ላይሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ የምናልፍባቸው ሁኔታዎች በጣም ከመክበዳቸው የተነሣ ለመደሰት ከባድ ይሆንብናል። በእነዚህ ጊዜያት አብርሃምን ለመምሰል እጥራለሁ። “ዘርህም እንዲሁ ይሆናል” ተብሎ ለእርሱ በተነገረው መሠረት፣ ምንም ተስፋ በሌለበት፣ አብርሃም በተስፋ አምኖ የብዙ ሕዝብ አባት ሆነ” (ሮሜ 4፥18)። ምንም ተስፋ በሌለበት፣ አብርሃም በተስፋ አመነ። በሌላ አባባል፣ ተስፋ ቢስ የሆነው ነገራችሁን ፊት ለፊት እየተመለከታችሁት፣ “ከእግዚአብሔር አትበልጥም! እርሱ የማይቻለውን ያደርጋል፤ ለሚያምኑት መልካም ሲያደርግ ደግሞ እጅግ ደስ ይለዋል፤ ስለዚህ ተስፋ መቁረጥ ሆይ! በእኔ ላይ አትሰለጥንም። በእግዚአብሔር እታመናለሁ!” በሉት።

እግዚአብሔርም ሁልጊዜ ያቺን ትንሿን የእምነት ጭላንጭል እንዳትጠፋ ይጠብቅልኛል። ከዚያም፣ ወዲያውኑ ባይሆንም እንኳ፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ላቀ ደስታና ልበ ሙሉነት ያቀጣጥላታል። በዚህ ሁሉ ውስጥ ኤርምያስ 32፥40-41 ይህንን ደስታ ያፋፍምልኛል።

“ለእነርሱ መልካም በማድረግ ደስ ይለኛል።” የታላቁ እግዚአብሔር ልብ ለእኔ እና ለእናንተ መልካም በማድረግ መደሰቱ በራሱ ምነኛ ያስደስታል!