“ስምዖን፣ ስምዖን ሆይ፤ እነሆ፣ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ጸለይሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ።” (ሉቃስ 22፥31–32)
ሌሎቹ ዐሥሩ ሐዋርያትስ (ይሁዳን ሳንቆጥር ማለት ነው)?
ሰይጣን እነሱንም ሊያበጥራቸው ነበር። ታዲያ ኢየሱስ ጸልዮላቸው ይሆን?
አዎ ጸልዮላቸዋል። ነገር ግን አብ የጴጥሮስን እምነት በጠበቀበት በተመሳሳይ መንገድ የእነርሱንም እምነት እንዲጠብቅ አልጠየቀም።
እግዚአብሔር የጴጥሮስን ትዕቢትና በራስ መታመን በዚያች በሰይጣን ወንፊት በተሰቃየበት ሌሊት ሰብሮለታል። መለሰው፤ ይቅር አለው፤ እንደቀድሞ አደሰው፤ እምነቱንም አጸና እንጂ አልተወውም። እናም አሁን የቀሩት አስሩን ማበርታት የጴጥሮስ ተልዕኮ ሆነ። “አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ።”
ኢየሱስ ጴጥሮስን በማበርታት ለዐሥሩ ብርታት ሆናቸው። የበረታው፣ የሚያበረታ ሆነ።
እዚህ ጋር ልናስተውለው የሚገባን ትልቅ ትምህርት አለ። አንዳንድ ጊዜ ጎህ ሳይቀድ፣ ማንም ከእንቅልፉ ሳይነሳ፣ እግዚአብሔር እምነታችሁን ለማጠንከር ከእናንተ ጋር በቀጥታ ይገናኛል። ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ (ከዐሥሩ – ዘጠኙን ጊዜ ማለት እንችላለን) እግዚአብሔር እምነታችንን ለማጠንከር ሌላን ሰው ይጠቀማል።
እግዚአብሔር በእምነት እንድንቀጥል የሚያስችለንን የጸጋ ቃል ወደ እኛ የሚያመጣን ስምዖን ጴጥሮስን ይልክልናል። “ሌሊቱን በልቅሶ ቢታደርም፣ በማለዳ ደስታ ይመጣል” የሚለውን የሚመሰክሩልን ሰዎች ይልክልናል (መዝሙር 30፥5)።
ዘላለማዊ ደህንነት በማህበር የሚሰራ ፕሮጀክት ነው። እግዚአብሔር በሰይጣን ማበጠሪያ እምነታችሁ እንደማይወድቅ ቃል በመግባት ልባችሁን ባበረታ ጊዜ፣ ያንን ቃል ያዙና በዚያው መበርታት ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን በማበርታት ደስታችሁን እጥፍ ድርብ አድርጉ።