እግዚአብሔር የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል | መስከረም 8

አምላኬም እንደ ታላቅ ባለጠግነቱ መጠን የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ይሞላባችኋል። (ፊልጵስዩስ 4፥19)

ፊልጵስዩስ 4፥6 ጳውሎስ፣ “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋር ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለማንኛውም ነገር አትጨነቁ” ይላል። ቀጥሎም በፊልጵስዩስ 4፥19 (ከ13 ቁጥሮች በኋላ) ወደፊት ስለሚገለጠው ጸጋ የሚናገረውን የነፃነት ተስፋ እንዲህ አስፍሮታል፦ “አምላኬም እንደ ታላቅ ባለጠግነቱ መጠን የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ይሞላባችኋል።”

ወደፊት ስለሚገለጠው ጸጋ የሚናገረውን ተስፋ በማመን የምንኖር ከሆነ፣ ጭንቀት ሊሰለጥንብን አይችልም። የእግዚአብሔር “የክብር ባለጠግነት” ማለቂያ የለውም። ይህን ሲል ስለወደፊት ሕይወታችሁ አትጨነቁ እያለን ነው።

ጳውሎስ ለእኛ ያስቀመጠውን ይህን ፈለግ መከተል አለብን። ካለማመን የተነሣ የሚመጣውን ጭንቀት፣ ወደፊት ስለሚገለጠው ጸጋ በሚናገረው ተስፋ መዋጋት አለብን።

ፈተና ስለሚበዛባቸው አንዳንድ ሥራዎች ስጨነቅ፣ አዘውትሬ ከማሰላስላቸው ተስፋዎች መካከል አንዱ የሆነውን ኢሳይያስ 41፥10ን ይዤ ካለማመን ጋር እዋጋለሁ።

በጀርመን ሐገር ሦስት ዓመታትን ለመቆየት ከአሜሪካ በወጣሁበት ቀን፣ አባቴ ስልክ ደውሎ ይህንን ቃል ሰጠኝ። በሦስት ዓመታት ውስጥ ከባድ የሆኑ የጭንቀት ጊዜያትን ሳሳልፍ፣ ብርታት እንዲሆነኝ ኢሳይያስ 41፥10ን ለራሴ ደጋግሜ ስነግረው ነበር፦ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፥ እረዳሃለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ እይዝሃለሁ።”

ጭንቀትን በዚህ የተስፋ ቃል ብዙ ጊዜ ስለተዋጋሁ፣ አእምሮዬ በሐሳብ ውጥረት መብዛት ጸጥ ሲልብኝ እንኳ፣ የኢሳይያስ 41፥10 ድምጽ ጎልቶ ይሰማኛል።