ዐይኖቼን ወደ ተራሮች አነሣሁ፤ ረድኤቴ ከወዴት ይመጣል? ረድኤቴ ሰማይንና ምድርን ከፈጠረ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይመጣል። እግርህ እንዲሸራተት አይፈቅድም፤ የሚጠብቅህም አይተኛም። (መዝሙር 121፥1-3)
እርዳታ ያስፈልጋችኋል? እኔ ያስፈልገኛል። ታዲያ ከወዴት እናገኘዋለን?
መዝሙረኛው ዓይኖቹን ወደተራሮች በማንሳት “ረድኤቴ ከወዴት ይመጣል?” ብሎ ከጠየቀ በኋላ፣ “ከእግዚአብሔር ዘንድ ይመጣል” ብሎ ይመልሳል — ከተራሮቹ ሳይሆን፣ ተራሮቹን ከሠራው ከእግዚአብሔር ዘንድ። “ረድኤቴ ሰማይንና ምድርን ከፈጠረ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይመጣል።”
እናም፣ ሁለት ታላላቅ እውነታዎችን ለራሱ ያስታውሳል፦ የመጀመሪያው፣ እግዚአብሔር በሕይወታችን በሚገጥሙን ችግሮች ሁሉ ላይ ብርቱ ፈጣሪ መሆኑን ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ እግዚአብሔር ፈፅሞ የማይተኛ መሆኑን ነው። “የሚጠብቅህም አይተኛም።”
እግዚአብሔር ድካም የሌለበት ሠራተኛ ነው። ፈፅሞ አይሰለችም። ታድያ እግዚአብሔርን በሕይወታችሁ ውስጥ እንደ ሠራተኛ አስቡት። በእርግጥም ያስደንቃል። ለእኛ የሚቀናን ራሳችንን በእግዚአብሔር ሕይወት ውስጥ ሠራተኞች አድርጎ መቁጠር ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በቅድሚያ እግዚአብሔር በእኛ ሕይወት ውስጥ የሚሠራውን እያየን እንድንገረም ይነግረናል። “ከጥንት ጀምሮ፣ በተስፋ ለሚጠባበቁት የሚደርስላቸው፣ እንደ አንተ ያለውን አምላክ ያየ ዐይን፣ ያደመጠ ጆሮ ፈጽሞ አልነበረም” (ኢሳይያስ 64፥4)።
እግዚአብሔር ያለማቋረጥ ለእኛ እየሠራ ነው። አያርፍም፣ ፈቃድ አይወጣም፣ ደግሞም አይተኛም። እንዲያውም፣ ለእኛ ለመሥራት ከመጓጓቱ የተነሳ፣ በእርሱ የሚያምኑትን እየዞረ ይፈልጋል። “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉና” (2ኛ ዜና መዋዕል 16፥9)።
እግዚአብሔር በእርሱ በሚታመኑት ላይ በመሥራት፣ የማይደክም ኃይሉን፣ ጥበቡን፣ እንዲሁም መልካምነቱን ማሳየት ይፈልጋል። እግዚአብሔር አብ፣ ልጁን ኢየሱስን፣ ወደ ምድር መላኩ የዚህ ዋነኛ ማሳያ ነው። “የሰው ልጅ ሊያገለግልና ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ መጣ እንጂ ሊገለገል አልመጣምና” (ማርቆስ 10፥45)። ኢየሱስ እርሱን ለሚከተሉት ይሠራል። ያገለግላቸዋል። የወንጌሉ ጥሪ፣ “ረዳት ሠራተኛ እንፈልጋለን” የሚል ጥሪ ሳይሆን፣ “እርዳታ እዚህ ይገኛል” የሚል አዋጅ ነው።
“ሁልጊዜ ደስ” እንዲላችሁ (1ኛ ተሰሎንቄ 5፥16)፣ “ስለ ሁሉ ነገር ሁልጊዜ” እንድታመሠግኑ (ኤፌሶን 5፥20)፣ እና “ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ” እንዲጠብቅላችሁ (ፊልጵስዩስ 4፥7) ከጓጓችሁ፣ “ ስለ ማንኛውም ነገር” እንዳትጨነቁ ከተመኛችሁ (ፊልጵስዩስ 4፥6)፣ በዚህ ዓለም ስትኖሩ ሕይወታችሁን ጠልታችሁ “ለዘላለም ሕይወት” ልትጠብቋት ከፈለጋችሁ (ዮሐንስ 12፥25)፣ እንዲሁም ጎረቤታችሁን እንደ ራሳችሁ በመውደድ መትጋት ከናፈቃችሁ (ማቴዎስ 22፥39)፣ ምስጢሩ ይህንን ታላቅ እውነት ማመን ነው።
ይህ እንዴት ያለ እውነት ነው! እግዚአብሔር ለሚጠብቁት ቀን እና ሌሊት ለመሥራት ዝግጁ ነው።