ይህን እያሰብን አምላካችን ለጥሪው የበቃችሁ አድርጎ እንዲቈጥራችሁ፣ መልካም ለማድረግ ያላችሁን ምኞትና ከእምነት የሆነውን ሥራችሁን ሁሉ በኀይሉ እንዲፈጽምላችሁ ዘወትር ስለ እናንተ እንጸልያለን። (2ኛ ተሰሎንቄ 1፥11)
ውሳኔዎቻችን እንዲፈጸሙ የእግዚአብሔርን ኅይል ስንፈልግ፣ የራሳችን ቁርጠኝነት የለንም ወይም መወሰን አንችልም ማለት አይደለም።
የእግዚአብሔር ኅይል የእኛን ነፃ ፈቃድ የሚተካ እና በቅድስና ጎዳና ውስጥ እንዲሁ ተሳታፊ የሚያደርገን አይደለም። ይልቅ በፈቃዳችን ዉስጥ እና ከፈቃዳችን በስተጀርባ የሚሰራ ልዩ የሆነ ኀይል ነው።
የእግዚአብሔር ኅይል በሕይወታችን ውስጥ የመኖሩ ማረጋገጫ የፈቃዳችን መወወገድ አይደለም። እንዲያውም የፈቃዳችን መሠረት ነው፤ በደስታ የምንታዘዝበት መሣሪያ ነው።
“በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ስለማምን ምንም ሳልሠራ እቀመጣለሁ” የሚል ማንም ቢኖር፣ ይህ ሰው በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት የማያምን ሰው ነው። ሰው በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት እያመነ እንዴት ነው እርሱን የማይታዘዘው?
ያለ ሥራ ስትቀመጡ በፈቃዳችሁ ያደረጋችሁት ድርጊት ነው። አለመሥራት በራሱ የኛን ውሳኔ የሚጠይቅ ሥራ ነው። ኅጢአትን እና ፈተናንም በዚህ መልክ ከሆነ የምትመለከቱት፣ በግልፅ አልታዘዝም እያላችሁ ነው፤ ምክንያቱም መልካሙን ገድል እንድትጋደሉ (1ኛ ጢሞቴዎስ 1፥18)፣ ዲያብሎስን እንድትቃወሙና (ያዕቆብ 4፥7)፣ ቅድስናን እንድትፈልጉ ታዝዛችኋል (ዕብራውያን 12፥14)። እንዲሁም እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ እንደምትሞቱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷችኋል (ሮሜ 8፥13)።
2ኛ ተሰሎንቄ 1፥11 መልካም ለማድረግ ያለንን ምኞት እና የእምነት ሥራዎቻችንን በእግዚአብሔር ኅይል እንደምናሳካ ይነግረናል። ይህ ማለት ግን “መልካም ለማድረግ ያለ ምኞት” እና “ሥራ” ይቀራሉ ማለት አይደለም። በእግዚአብሔር ጥሪ ውስጥ በቅቶ የመገኘት አንዱ አካል እኛ በፈቃዳችን የጽድቅ ሥራን ለመስራት ያለን ተነሳሽነት ነው።
በሕይወታችሁ ውስጥ የሚደጋገም ኅጢአት ካለ፣ ወይም ልትሰሩት የሚገባን መልካም ሥራ በቸልተኝነት ያለ ምንም ትግል እንዲሰራላችሁ የምትጠብቁ ከሆነ፣ አለመታዘዛችሁ ላይ እየከመራችሁበት ነው። እግዚአብሔር በፈቃዳችሁ ውስጥ በኀይል የሚገለጠው በእናንተ መልካም የማድረግ ፍላጎት እና ፈቃድ ውስጥ አልፎ ነው።
ስለዚህ በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት የሚያምኑ ሰዎች ለቅድስና በሚያደርጉት ትግል ውስጥ የግል ውሳኔ ለማድረግ እና ፈቃዳቸውን ለመቆጣጠር መፍራት የለባቸውም። “በጠባቧ በር ለመግባት ተጣጣሩ፤ እላችኋለሁ፤ ብዙዎች ለመግባት ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን አይሆንላቸውም” (ሉቃስ 13፥24)። ስለዚህም ተጣጣሩ! እንደ በጎ ፈቃዱ መፈለግንና ማድረግን በእናንተ መጣጣር ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር መሆኑን በማመን ለመልካም ስራ ሁሉ ተጣጣሩ (ፊልጵስዩስ 2፥13)።