ለገዛ ልጁ ያልሳሳለት፣ ነገር ግን ለሁላችንም አሳልፎ የሰጠው እርሱ፣ ሁሉንስ ነገር ከእርሱ ጋር እንደ ምን በልግስና አይሰጠን? (ሮሜ 8፥32)
ለሁሉም ደራሽ የሆነው የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል የሚገኘው ሮሜ 8፥32 ላይ ነው። ይህ ለእኔ የመጽሐፍ ቅዱስ ውዱ ቃል ነው። ለዚህ አንዱ ምክንያት ይህ የተስፋ ቃል ሁሉን አካታች ከመሆኑ የተነሣ በሕይወቴ እና አገልግሎቴ ሁሉ ስለሚጠቅመኝ ነው። ይሄ የተስፋ ቃል እኔን ያልጠቀመበት ጊዜ አልነበረም፤ አይኖርምም።
ይህ የተስፋ ቃል ብቻውን ሲታይ ልዩ እና ውድ ላይመስል ይችላል። ሌሎችም ዘመን የማይሽራቸው የተስፋ ቃሎች አሉ፦ “እግዚአብሔር በቅንነት የሚሄዱትን፣ መልካም ነገር አይነፍጋቸውም” (መዝሙር 84፥11) ወይም “እንግዲህ ማንም በሰው አይመካ። ሁሉ ነገር የእናንተ ነውና፤ ጳውሎስም ሆነ አጵሎስ ወይም ኬፋ፣ ዓለምም ሆነ ሕይወት ወይም ሞት፣ አሁን ያለውም ሆነ ወደ ፊት የሚመጣው፣ ሁሉ የእናንተ ነው፤ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ፤ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው” (1ኛ ቆሮንቶስ 3፥21-23)። የእነዚህን ተስፋዎች ስፋት እና ጥልቀት፣ እንዲሁም በአማኞች ሕይወት ውስጥ ያላቸውን ወሳኝነት በቃላት መግለጽ ከባድ ነው።
ሆኖም ግን ሮሜ 8፥32ን ለየት የሚያደርገው የተመሠረተበት ዐለት ነው። የተስፋ ቃሉ እግዚአብሔር ለልጁ እንዳለው ፍቅር ሁሉ በማይነቃነቅ መሠረት ላይ የቆመ ነው።
ይህ ጥቅስ የያዘው መሠረት እና እርግጠኝነት እጅግ ጽኑ እና የተረጋገጠ በመሆኑ፣ የተስፋ ቃሉ በፍጹም ሊሻር ወይም ሊፈርስ አይችልም። በነውጥ ጊዜ የሚያጠነክረን እና ብርታት የሚሆነን ለዚህ ነው። በሕይወታችን ውስጥ ሁሉም ነገር ቢጠፋ፣ ሁሉም ነገር ቢለዋወጥ፣ ሁሉም ነገር ቢበላሽ፣ ይህ ሁሉን የሚጠቀልል የወደፊት የተስፋ ቃል በፍጹም አይወድቅም።
ታዲያ ይህ መሠረት ምንድን ነው? “ለገዛ ልጁ ያልሳሳለት፣ ነገር ግን ለሁላችንም አሳልፎ የሰጠው እርሱ…” መሠረቱ ይህ ነው። አንድያ ልጁን ሳይሰስት ሰጥቶናል! ታዲያ ይህ እውነት ከሆነ ይለናል የእግዚአብሔር ቃል፣ በሙሉ እርግጠኝነት ልጁን ለሰጣቸው ሁሉ ሁሉንም ነገር አሳልፎ ይሰጣቸዋል ማለት ነው!