በእርሱ በኩል ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና እያቀረባችሁ፣ በቃልም ሆነ በተግባር የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት። (ቈላስይስ 3፥17)
በጣም የሚያስፈልጋችሁ ነገር ጠፍቶባችሁ፣ እናንተ ግን በተሳሳተ ቦታ በመፈለግ ስትደክሙ፣ “እግዚአብሔር ምን እየሠራ ይሆን?” ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ? በትክክል የት እንዳለ ያውቃል፤ ነገር ግን ሆን ብሎ በሌለበት ቦታ እንድትፈልጉ እያደረጋችሁ ነው።
በአንድ ወቅት “Desiring God” የተሰኘውን መጽሐፌን ስጽፍ፣ ለማካተት የፈለግሁት የሪቻርድ ውርምብራንድን አባባል ነበር። የገመትኩት “Reaching Toward the Heights” በተሰኘው የጥሞና መጽሐፉ ውስጥ ይኖራል ብዬ ነበር። ሙሉ መጽሐፉን ባገላብጥም፣ ላገኘው ግን አልቻልኩም።
ታዲያ ይህን የጠፋኝን ጥቅስ ፍለጋ ሳነብ፣ ህዳር 20 ላይ ባለው ጥሞና ልቤ ተወሰደ። “በተሳሳተ ቦታ ጥቅሱን እንድፈልግ ጌታ ያደረገኝ ለዚህ ነው” አልኩ። ያነበብኩት ታሪክ፣ በኢየሱስ ስም የምናደርገው ማንኛውም ነገር — በተሳሳተ ቦታ ጥቅስ መፈለግ እንኳ ቢሆን — ለከንቱ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነበር። እንዲህ ይላል፦
ካትሪን የአእምሮ ዝግመት ላለባቸው ልጆች በተዘጋጀ ቤት ውስጥ ነበር ለ20 ዓመታት የኖረችው። ከተወለደች ጀምሮ አንዲት ቃል ተናግራ አታውቅም። ወይ በጸጥታ ግድግዳ ላይ ታፈጣለች አልያም ለመንቀሳቀስ ትዳክራለች። ሙሉ ሕይወቷ መብላት፣ መጠጣት እና መተኛት ነበር። አንድ እግሯም መቆረጥ ነበረበት። ተንከባካቢዎቿም ጌታ ወደ እራሱ እንዲወስዳት ይመኙላት ነበር።
ታዲያ አንድ ቀን ዶክተሯ ዳይሬክተሩን በፍጥነት እንዲመጣ ይጠራዋል። ካትሪን እየሞተች ነበር። ወደ ክፍሏ ሲገቡም ያዩትን ማመን አቃታቸው። ካትሪን ሲዘመሩ ሰምታ በቃሏ የያዘቻቸውን፣ በሞት አፋፍ ላይ የሚዘመሩ መዝሙሮችን ደጋግማ እየዘመረች ነበር። ለግማሽ ሰዓት ያክል ፊቷ ተለውጦ እያበራ፣ “ነፍሳችን እረፍቷን፣ አባት ሃገሯን የት ታገኛለች?” የሚልን ጀርመንኛ ዝማሬ ደጋግማ ደጋግማ ከዘመረች በኋላ በሰላም አረፈች።
The Best Is Still to Come, Wuppertal: Sonne und Shild
በእርግጥ በክርስቶስ ስም ተደርጎ ከንቱ የሚሆን ነገር ይኖር ይሆን? በፍጹም!
ያስፈለገኝ መስሎኝ ስፈልግ የደከምክሁት በከንቱ አልባከነም። ለዚህች ልጅ የተዘመሩላት መዝሙሮችም በፍጹም አልባከኑም። ወደ ጌታ ያልተጠበቀ ሥራ ከተመለከታችሁ፣ እንዲሁም ሁሉንም ነገር በስሙ ካደረጋችሁ፣ የእናንተም ያልታቀደ አታካች እና አድካሚ መንገድ በፍጹም አይባክንም (ቈላስይስ 3፥17)።