የእግዚአብሔር የመጨረሻ እና ወሳኝ ቃል | ጥቅምት 16

እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በተለያየ ጊዜና በልዩ ልዩ መንገድ በነቢያት በኩል ለአባቶቻችን ተናግሮ፣ በዚህ መጨረሻ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገውና ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ ለእኛ ተናገረን። (ዕብራውያን 1፥1-2)

የመጨረሻው ዘመን የሚጀምረው በልጁ ወደዚህ ዓለም መምጣት ነው። “በዚህ መጨረሻ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገውና ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ ለእኛ ተናገረን” ይላል። ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ከመጣበት ጊዜ አንሥቶ የእግዚአብሔር መንግሥት በሙላት እስከምትመጣበት ጊዜ ድረስ የመጨረሻው ዘመን ሲሆን፣ እኛም በዚህ ጊዜ ውስጥ እየኖርን ነው።

የዕብራውያን ጸሐፊ መልእክት ይህ ነው፦ እግዚአብሔር በልጁ የተናገረው ቃል የመጨረሻ ውሳኔው ቃል ነው። በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ መሪነት ይህ ቃል በአዲስ ኪዳን ጽሑፎች ውስጥ ተዘግቧል። የሚመጣውም ትውልድ ከእግዚአብሔር ሌላ ቃል ይወጣ ይሆን እያለ በማለም እንዳይቅበዘበዝ በግልጽ ጥበቃውን አኑሯል። ይህ ቃል ከዚህ በኋላ በሚመጣ በሌላ ቃል አይተካም። የኢየሱስ ማንነት፣ የኢየሱስ አስተምህሮና የኢየሱስ ሥራ ሁሉ አዲስ ኪዳን ብለን በምንጠራው በዚህ ሐዋሪያዊ ጽሑፍ ውስጥ ተካቷል። እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።

“እግዚአብሔርን መስማት ፈልጌ ነበር፤ ግን እግዚአብሔር በግልጽ አይናገረኝም” እያልኩ ሳጉረመርም ምን እያልኩ ነው? እውነት ይህንን በአዲስ ኪዳን የተጻፈውን የመጨረሻ (ወሳኙ) ቃል በሙሉነት እንደተገለጠበት ያህል ተጠቅሜ ጨርሼዋለሁ ወይም ገብቶኛል ማለት ነው? በውኑ ቃሉን ተረድቼ ጨርሻለሁ? ከኔ ጋር ከመዋሃዱ የተነሣ የሕይወቴ ምሪት ሁሉ ከሱ የመነጨ ነው ማለቴ ነው?

ወይስ እንደ ቀላል ነገር አይቼዋለሁ ማለት ነው? ጋዜጣ እንደማነበው ወይም ፌስቡክ እንደምጠቀመው፣ እዚህም እዚያም እያልኩ ሲስለቸኝ የተለየ ነገር ፍለጋ እየወጣሁ ነው? የምመለከተው እንዲህ አይደለም ብል ውሸት ይሆንብኛል።

እግዚአብሔር የመጨረሻውን፤ ወሳኙን እና ማለቂያ የሌለውን ቃሉን እንድንሰማ ይጠራናል። ውስጣችን ገብቶ እስከሚዋሃደን ድረስ እንድናሰላስለው እና እንድናጠናው፤ ራሳችንን በቃሉ ውስጥ እንድንዘፍቅ፣ እንድንሸመድደው ጭምር ይነግረናል።