“እንደ ታማኝ የእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢ እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል” (1ኛ ጴጥሮስ 4፥10)።
መንፈሳዊ ስጦታዎቻችንን ስንጠቀም፣ እንደ ባለአደራ እየመነዘርን ያለነው የእግዚአብሔርን ጸጋ ነው። ይህም ጸጋ ያለፈ ጸጋ ሳይሆን ለዛሬ የተመደበልን ጸጋ ነው። ይህ የወደፊት ጸጋ ከሰው ሰው ይለያያል። ለእያንዳንዱ ሰው የተሰጠው ጸጋ “ልዩ ልዩ” ነው። ለአካሉ የተሰጡ መንፈሳዊ ስጦታዎች እጅግ የተለያዩ ከሆኑባቸው ምክንያቶች አንዱ ነው። የእግዚአብሔር ጸጋ በአንዳችን ሕይወት ሲያልፍ የሚያንጸባርቀው መለኮታዊ ክብር በሌላችን ሲያልፍ ከሚያንጸባርቀው ጋር ይለያያል። በእያንዳንዱ ሕይወት ውስጥ ልዩ በሆነ መንገድ ይገለጣል።
በክርስቶስ አካል ውስጥ ለወደፊት እጅግ የሚያስፈልጉ በርካታ ጸጋዎች አሉ። በሚያስፈልገን ልክ እና እንዲያውም ከሚያስፈልገንም በላይ የተመደቡ ጸጋዎች አሉ። የመንፈሳዊ ስጦታዎች ዓላማ እነዚህን ጸጋዎች ከላይ በመቀበል በሚያስፈልጉን ልክ ማከፋፈል ነው።
ምናልባት አንድ ሰው፣ የጴጥሮስ ንግግር ከወደፊት ጸጋ ጋር ያለውን ግንኙነት ሊጠይቅ ይችላል። ባለአደራ እኮ የሚያስተዳድረው ቀድሞውኑ በእጁ የተሰጠውን ንብረት እንጂ፣ ወደፊት የሚቀርብለትን አይደለም ሊል ይችላል።
ወደ ፊት የሚገለጠውን ጸጋ ለማመልከት ጴጥሮስን የተጠቀምኩበት ዋናው ምክንያት፣ የሚቀጥለው ቁጥር ይህ እንዴት እንደሚሰራ ስለሚገልጽ ነው። ይህ ጥቅስ የወደፊት ጸጋ ቀጣይነት ያለው እንደሆነ ያብራራል። እንዲህ ይላል፦ “ከእናንተ ማንም የሚናገር ቢኖር እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢኖር እግዚአብሔር በሚሰጠው ብርታት ያገልግል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንዲከብር ነው፤ ክብርና ኀይል ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን፤ አሜን” (1ኛ ጴጥሮስ 4፥11)። አያችሁ? “በተሰጠው” ሳይሆን “በሚሰጠው” ነው የሚለው። ወደፊት ነው የሚሰጠው። በአገልግሎታችሁ ሁሉ፣ ከሥር ከሥር በሚሰጣችሁ ቀጣይነት ባለው የእግዚአብሔር የጸጋ ኃይል አገልግሉ።
ነገ የሆነን ሰው ለማገልገል መንፈሳዊ ስጦታችሁን ስትጠቀሙ፣ የምታገለግሉት እግዚአብሔር በሚሰጣችሁ ኀይል ነው። የሚደርሳችሁም ነገ እንጂ ዛሬ አይደለም። ቃሉ እንደሚል፤ “እንደ ዕድሜህ እንዲሁ ኃይልህ ይሆናል” (ዘዳግም 33፥25 ቀ.ኃ.ሥ)።
አምላካችን እግዚአብሔር እርሱን የምናገለግልበትን አቅም እና ብርታት ቀን በቀን፣ ሰዓት በሰዓት ይሰጠናል። ይህን የሚያደርገውም ክብርን ስለሚያገኝ ነው። የማይቋረጠው ጉልበቱ እና የማይዝለው ክንዱ በሚሰጠን ጸጋ እርሱ ይከብራል። ስለዚህ፣ “የሚያገለግል ሁሉ እግዚአብሔር በሚሰጠው ብርታት ያገልግል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንዲከብር ነው፤ ክብርና ኀይል ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን፤ አሜን።”