እግዚአብሔር በእናንተ ደስታን ያገኛል?
ሲመለከታችሁስ ፈገግ ይላል?
በአጭሩ፣ ክርስቲያን ከሆናችሁ መልሱ አዎን ነው። ይሁን እንጂ እንዴት እና ለምን እንዲሁም በምን መሠረት ለሚሉት ጥያቄዎች መልስና ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል።
እግዚአብሔር በተቤዣቸው ላይ ያለውን ደስታ በሦስት ልንከፍለው እንችላለን፦ (1) በምርጫው ያለው ደስ መሰኘት (2) በመቤዠት ያለው ደስ መሰኘት (3) በቅድስና ያለው ደስ መሰኘት
- በምርጫ ያለው ደስ መሰኘት
በመጀመሪያ እግዚአብሔር በልጆቹ ደስ መሰኘቱን በምርጫ ውስጥ ገልጿል። ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በነፃ፣ ያለ ምንም ኢ-ፍትሐዊነት ያለ አድልዎ በተወሰኑ ነፍሶች ላይ ደስታውን ያኖር ዘንድ እግዚአብሔር መረጠ። ይህም ደስታው የአሀዱ ሥሉስ አምላክ ደስታ ነጸብራቅ ነው (ሉቃስ 10፥21)።
ለመቤዥት እና ልጆች አድርጎ በቤተሰቡ ውስጥ ለመቀበል የተወሰኑ ሰዎችን በነፃ በመምረጡ እግዚአብሔር ደስ ይለዋል (ሮሜ 9፥10-18፤ ኤፌሶን 1፥3-6)።
በምርጫ ውስጥ የታየው ይህ አስቀድሞ የተወሰነ ደስታ በእኛ ውስጥ ባለ አንዳች ነገር ላይ የተመሠረተ አይደለም።
- በመቤዠት ያለው ደስ መሰኘት
በመቀጠል የመረጣቸው በክርስቶስ በኩል ቤዛነት በማግኘታቸው እግዚአብሔር ደስ ይለዋል (ሉቃስ 15፥7)። ይህ ደስታ የተንጠለጠለው በክርስቶስ ፍጹም ሥራ ላይና በእምነት አማካኝነት ይህ ሥራ ለምርጦቹ በስፍራና ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ መሆኑ ላይ ነው። ለድነት የሆነው እምነታችን መታየቱ ሳይቀር እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል (ዕብራውያን 11፥6)። ጽድቅ ከሚጠብቅባቸው የሕግ ድንጋጌዎች ነፃ ወጥተው ከክርስቶስ ጋር ባላቸው አንድነት ለዘላለም ሲጸድቁ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የደስታን መዝሙር ይዘምራል (ሶፎንያስ 3፥14-17)።
አንድ ኀጢአተኛ ሲቤዥ በሰማይ ያሉ መላእክት የሚኖራቸውን ደስታ አስቡ። እንዲሁም የጠፋው ልጁ ሲመለስ አባት የተሰማውን የተትረፈረፈ ፌሽታ እና ደስታ አስቡ። በተመሳሳይ ሁኔታ የተመረጡት ሲድኑ እግዚአብሔር ለዘላለም በእናንተ ደስ ሊለው ልቡ ወደ እናንተ ዘንበል ይላል (ሉቃስ 15፥11-24)።
- በቅዱስ መታዘዝ ያለው ደስ መሰኘት
በሦስተኛነት እግዚአብሔር እውነተኛ በሆነ መታዘዝ ደስ ይለዋል።
በአጽናፈ ዓለማችን ውስጥ ካሉ ምስጢራዊና ድንቅ የሆኑ እውነታዎች መካከል አንዱ፣ ኢየሱስ ሰው ሆኖ ከመጣና እያደገ ከሄደ በኋላ አብ በኢየሱስ ያለው ደስ መሰኘት እያደገ መሄዱ ነው (ሉቃስ 2፥52)። እስቲ አስቡት፣ ለአባቱ ፍቃድ በመታዘዙ ወልድ በአብ ደስታ ውስጥ ይኖር ነበር (ዮሐንስ 10፥18፣ 12፥49፣ 14፥31፣ 15፥10)። እጅግ ከሚያስደንቁኝ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ውስጥ አንዱ ነው።
ይሁን እንጂ ምንም ሚስጥር ያልሆነው ነገር የምንከተለው የኢየሱስ የመታዘዝ ፈለግ ነው። በመታዘዛችን ደግሞ በእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ እንኖራለን። እግዚአብሔርም በቅድስናችን ደስ ይለዋል (ዮሐንስ 14፥21-24)።
በእውነተኛ መታዘዝ ውስጥ አብሮን የሚኖር የክርስቶስን ፍቅር እንዲሁም እየጨመረ የሚሄድን የእግዚአብሔር ደስታ እንለማመዳለን (ዮሐንስ 15፥9-11)።
ለምሳሌ፣ ትሕትና ውብ በሆነ ሁኔታ እግዚአብሔርን ይስበዋል። ትሕትና ዐይኖቹን ይማርካል። የተሰበረ ትሑት ልብ እግዚአብሔርን አቅርቦ በመሳብ ደስ እንዲለው ያደርገዋል (ያዕቆብ 4፥8-10፣ ኢሳይያስ 57፥15፣ 66፥2፣ መዝሙር 34፥18)።
ኀጢአት የሚሠራው በተቃራኒ አቅጣጫ ነው። ደስታ ከሐዘን ተቃርኖ የሚቆም ነው። ስለዚህም እንደ ማንኛውም ልጆቹን የሚወድድ አባት እግዚአብሔር በኀጢአታችን ከልቡ ያዝናል (ኤፌሶን 4፥30፣ ዕብራውያን 12፥3-11)። በውስጣችን ያለ አለመታዘዝ ለእኛ ያለውን ዘላለማዊ የመቤዠት ዓላማ ተጻርሮ ይቆማል። ባለመታዘዛችን ውስጥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ኀጢአት የበለጠ አስደሳች ነው ብለን ተጨባጭ በሆነ ሁኔታ እያወጅን ነው። እንዲህ ያለው ርምጃ እንዴት አያምመውም?
ልጆቹን የመረጠ እና የተቤዣቸው አባት በኀጢአታችን ከልቡ ያዝናል፤ እንዲሁም በቅድስናችን ከልቡ ደስ ይሰኛል።
አንድ ዓላማ
ታዲያ እነዚህ ሦሰት ደስታዎች በአንድነት የሚቆሙት እንዴት ነው?
ቁልፉ ነገር እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያለውን ደስታ እንደ ሦስት የተለያዩ ደስታዎች ከማየት የአንድ ደስታ ሦስት ደረጃዎች አድርጎ መረዳት ነው። በሌላ አገላለጽ፣ ሦስቱም በአንድ እቅድ ውስጥ ተያይዘው ይቆማሉ። እግዚአብሔር በምርጫ (1) ያለው ደስታ፣ በመቤዠት (2) ወዳለው ደስታው ይመራል፤ ይህም ደግሞ በመታዘዛችን (3) ወዳለው ደስታ ይመራል።
በእያንዳንዱ ደረጃ፣ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያለው ደስታ በጊዜ ውስጥ እያደገ እና እየጠነከረ፣ ደግሞም የበለጠ እየተቀጣጠለ እንደሚመጣ እሳት በግብረገባዊ ድምቀት እና ፍጹም ክርስቶስን ወደ መምሰል አቋም የሚያድግ ነው (1ኛ ዮሐንስ 3፥2)።
በሌላ አገላለጽ፣ ሪቻርድ ጋፊን እንዳለው በመክበራችን ውስጥ ፍጹም የሚሆነው የመቀደሳችን ሂደት፣ አስቀድሞ በመወሰናችን ውስጥ የታለመው ዓላማ ነው። የተመረጥነው እና የተዋጀነው በሙሉ ሰውነታችን የእግዚአብሔርን ክብር በሚገባ የምናንጸባርቅ ፍጥረቶች እንድንሆን ነው። የእግዚአብሔር ምርጫ እና ቤዝዎት በክብር መቋጫ ማግኘቱ፣ እንደ ኤፌሶን 1፥3-10 እና ሮሜ 8፥29-30 ባሉ ታላላቅ ጽሑፎች ጭብጥ ውስጥ የሚገኝ ነው።
እግዚአብሔር በልጆቹ ላይ ያለው ደስታ በምርጫው ላይ በመመሥረት ጠንካራ እና ቋሚ የሆነ በቤዝዎት አፈጻጸም ውስጥ ላይናወጥ የተጠበቀ፣ ከእውነተኛ ቅድስናችን እና ፍቃዱን ከመፈጸማችን አንጻር የሚያድግ፣ አድጎም አንድ ቀን ለእርሱ ታላቅ ደስታ ይሆንለት ዘንድ ፍጹም የሚሆን ነው!
ተደነቁ!
በክርስቶስ የሆነ ማንኛውም ሰው፣ ይህንን የእግዚአብሔር ዕቅድ ተመልክቶ መደነቅ ይችላል።
በመጀመሪያ፣ ክብሩን ከፍ ያደርጉ ዘንድ እግዚአብሔር ሰዎችን ፈጠረ። እኔን ፈጠረኝ። እርሱን ችላ ብዬ፣ በዚያ ምትክ ኀጢአትን መረጥኩ። ይሁን እንጂ፣ እኔ ባላውቅም፣ ዓለም ሳይፈጠር ልዩ ፍቅሩን በእኔ ላይ አኖረ። ውብ በሆነው መታዘዙ እኔን በስሜ ይቤዠኝ ዘንድ ክርስቶስ ሊኖር እና ሊሞት ወደ ዓለም መጣ። እኔን ለማጽደቅ፣ መንፈሱንም ይሰጠኝ ዘንድ፣ ፍጹም ቆሻሻ ከሆንኩት ከእኔ ውስጥ ዳግም ውብ የሆነን ፍጹም የሚታዘዝ፣ በቅድስና የደመቀ፣ ከእግዚአብሔር ጋር በቅዱስ ኅብረት ደስ የሚለው ማንነት ይፈጥር ዘንድ ክርስቶስ ወደ ዓለም መጣ። አሁን ላይ ያለኝ ኀጢአት እና አለመታዘዝ ያሳምመዋል። ይሁን እንጂ፣ ከኀጢአት ጋር በማደርገው እያንዳንዱ ፍልሚያ እንዲሁም ለመታዘዝ በማደርገው መጣጣር ደስ ይለዋል። የአዳኜን ክብር በውስጥ መነሣሣቴ፣ አሳቤ፣ በቃላቴ ሁሉ እና በድርጊቴ ማንጸባረቅ ወደምችልበት ቀን በፍቅር ይመራኛል። በዚህም ደስ ይለዋል። እግዚአብሔር የፈጠረኝ እንዲህ እንድሆን ነው!
ዛሬ ላይ ይህ ያሰፈልገናል። ኬቨን ዲያንግ እንደሚለው፣ “ለመታዘዝ ዋነኛው መነሣሣት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው ነገር መሆኑ ነው።”
ወይም ጆን ፓይፐር እንደሚለው፣ “መታዘዛችን በእርሱ ደስ የመሰኘታችን ፍሬ ሲሆን፣ እግዚአብሔር በመታዘዛችን ደስ ይሰኛል። መታዘዛችን የእኛ የከበረው ነገር እግዚአብሔር መሆኑን ሲመሰክር፣ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝበት ይሆናል።”
በቶኒ ሬንክ