መልካም ያደርግልህ ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ | ጳጉሜ 1

“እናንተ አነስተኛ መንጋ የሆናችሁ፤ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ መልካም ፈቃድ ነውና አትፍሩ።”  (ሉቃስ 12፥32)

በእምነታችን በደከምን ጊዜ፣ ኢየሱስ ባለማመናችን እንድንጸና እንዲሁ አይተወንም። ይልቁንም በእምነት ትግል ውስጥ ላለን ሁሉ፣ በቃሉ በኩል በኀይል ይናገረናል።

እግዚአብሔር ለእኛ መልካም ሊሆንልን የሚፈልግ አምላክ እንዳልሆነ የሚነግረንን ፍርሃት እንድናሸንፍ ይፈልጋል። አምላካችን ቸርና ሩኀሩኀ፣ መኀሪና ለጋስ ሳይሆን፣ በኀጢአታችን የሚጸየፈን ቁጡና ችኩል አምላክ ነው ብለን እንዳናስብ ማድረግ የጌታ ኢየሱስ ዓላማ ነው።

ምንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር መልካም እንደሆነ በአእምሮአችን ብናምንም፣ በልባችን ግን የግዱን ቸር እንደሆነና መልካምነቱም የተገደበ እንደሆነ ሊሰማን ይችላል። ልክ አንድ ዳኛ ተከሳሹ ላይ ሊፈርድበት ፈልጎ፣ ነገር ግን የተከሳሹ ጠበቃ ያልጠበቀውን አንቀጽ ጠቅሶበት ያለፍላጎቱ በነጻ ለማሰናበት እንደተገደደ፣ እኛም የእግዚአብሔርን ምሕረት እንደዚያ የምንቆጥርበት ጊዜ ይኖራል።

ነገር ግን እግዚአብሔር እንዲህ እንደሆነ እንዳናስብ ኢየሱስ ታላቅ ዋጋ ከፍሏል። በሉቃስ 12፥32 እግዚአብሔር መንግስቱን ለእኛ በመስጠቱ ውስጥ ያለውን ታላቅ ደስታ በማሳየት አፍቃሪነቱን እና ምነኛ ግሩም የሆነ ልብ እንዳለው ይገልጽልናል።

“እናንተ አነስተኛ መንጋ የሆናችሁ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ መልካም ፈቃድ ነውና አትፍሩ” በሚለው አስደናቂ አረፍተ ነገር ውስጥ ያሉት እያንዳንዱ ቃላት፣ ኢየሱስ የሚያውቀውና የሚረዳውን ፍርሃታችንን እና ትግላችንን ለማስወገድ ታስበው የተነገሩ ናቸው። እግዚአብሔር መልካም ነገርን ሲያደርግ የሚያደርገው ያለፍላጎቱ ከራሱ ጋር እየተጋጨና እየተቆጣ ነው የሚል ከንቱ እሳቤን ያፈርሳል።

ሉቃስ 12፥32 የሚናገረው ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ ነው። የእግዚአብሔር ልብ ምን እንደሚመስልና ምን ደስ እንደሚያሰኘው ይገልጥልናል። ወደፊት ስለሚያደርገውና ማድረግ ስለሚጠበቅበት ነገር ብቻ ሳይሆን፣ ማድረግ ስለሚወደውና በማድረጉም ደስ ስለሚሰኝበት ነገር ያበስረናል። እያንዳንዱ ቃል ልዩ ዋጋ አለው። “እናንተ አነስተኛ መንጋ የሆናችሁ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ መልካም ፈቃድ ነውና አትፍሩ።”