በእውነተኛ ልብ … እንቅረብ። (ዕብራውያን 10፥22)
በዚህ ክፍል የተሰጠን ትዕዛዝ ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ ነው። የዕብራውያን መጽሐፍ ጸሐፊ ትልቁ ዓላማ ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ፣ ከእርሱ ጋር ኅብረት እንድንፈጥር፣ ከእግዚአብሔር ከራቀ ክርስቲያናዊ ሕይወት ጋር እንዳንስማማ ነው።
ይህ መቅረብ አካላዊ ድርጊት አይደለም። ወደ መንግሥተ ሰማይ ለመድረስ በራሳችን የባቢሎንን ግንብ መገንባት አይደለም። የግድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ መሄድም አይደለም። ወይም ከፊት ለፊት ወዳለው የአዳራሹ መድረክ መሄድ አይደለም። የማይታይ የልብ ተግባር ነው። በዝምታ ቆማችሁ፣ ወይም በሆስፒታል አልጋ ላይ ተኝታችሁ፣ አልያም ደግሞ ወደ ሥራ ለመሄድ ባቡር ውስጥ ሆናችሁ ማድረግ የምትችሉት ነው።
የወንጌል ማዕከላዊ ሐሳብ ይህ ነው፤ የጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ እና የስቅለት ቀን የሚያወሩትም ይህንኑ ነው። እግዚአብሔር እኛን ወደ ራሱ ለማቅረብ አስደናቂ የሆነን ዋጋ ከፍሏል። በእርሱ በኩል እንድንቀርብ ልጁን መከራ እንዲቀበልና እንዲሞት ልኮታል። በታላቁ የቤዛነት ዕቅድ ውስጥ ያደረገው ነገር ሁሉ እኛ ወደ እርሱ እንድንቀርብ ነው። ያ ቅርበት ደግሞ ለደስታችን እና ለክብሩ ነው።
ለእርሱ አናስፈልገውም። በመራቃችን እርሱ ደሃ አይሆንም። በሥላሴ ኅብረት ደስተኛ እንዲሆን እኛ አናስፈልገውም። ነገር ግን፣ ኃጢአተኞች ብንሆንም እንኳ፣ ነፍሳችንን ሙሉ በሙሉ እና ለዘላለም ወደ ሚያረካው አንድ እውነታ፣ ማለትም ወደ እራሱ፣ በልጁ በኩል በነፃ እንድንደርስ በማድረግ ምህረቱን ያጎላዋል። “በአንተ ዘንድ የደስታ ሙላት፣ በቀኝህም የዘላለም ፍሥሓ አለ” (መዝሙር 16፥11)።
ይህን እንኳ ስታነቡ ለእናንተ የእግዚአብሔር ፈቃድ ይህ ነው። ክርስቶስም የሞተው ለዚህ ነው፦ ወደ እግዚአብሔር ትቀርቡ ዘንድ ነው።