ጥበብ የተሞላው የእግዚአብሔር ምሕረት | ጥቅምት 3

እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ መሰናክል፣ ለአሕዛብ ደግሞ ሞኝነት ነው። እግዚአብሔር ለጠራቸው ግን፣ አይሁድም ሆኑ ግሪኮች፣ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኀይል፣ የእግዚአብሔርም ጥበብ ነው። (1ኛ ቆሮንቶስ 1፥23-24)

የአምላክ ቁጣ ማረፊያ መሆናችን፣ ጻድቅ ከመሆኑም የተነሣ ክብሩን ስለማያስደፍር ዘላለማዊ ቁጣውን በኅጢአታችን ላይ እንደሚያፈስ የሚናገረውን አስፈሪ አዋጅ የሚሽር አስደናቂ የምሥራች ዜና አለ።

ይህን እውነት ማንም በተፈጥሮ ውስጥ ሊማረው እና ሊደርስበት አይችልም። ይህ የወንጌል እውነት ለጎረቤቶቻችን መነገር፣ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት መሰበክ እና በሚሲዮናውያን መዳረስ አለበት።

መልካሙ ዜና ይህ ነው፦ እግዚአብሔር በሰው ልጆች ሁሉ ላይ መፍረዱን ትቶ፣ የእርሱን ፍትሕ መፈጸም የሚቻልበት መንገድን አሰናድቷል የሚል ነው።

ሲኦል ከኅጢአተኞች ጋር ሒሳቡን የሚያወራርድበት እና ፍትሕ የሚሰፍንበት መንገድ ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር ሌላ መንገድ አዘጋጅቷል፤ ይህም ወንጌል ነው።

እግዚአብሔር በጥበቡ፣ ፍትሕ ሳይጓደል ፍቅሩ ከቁጣው ሊያድነን የሚችልበትን መንገድ አበጅቷል። ይኸው! ይህ ነው ወንጌል። አስረግጬ በድጋሚ ልበለው። እግዚአብሔር በጥበቡ፣ ፍትሕ ሳይጓደል ፍቅሩ ከቁጣው ሊያድነን የሚችልበትን መንገድ አበጅቷል።

ይህ ጥበብ ምንድነው? የእግዚአብሔር ልጅ ለኅጢአተኞች ሲል መሞቱ ነው! “እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን… ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኀይል፣ የእግዚአብሔርም ጥበብ ነው” (1ኛ ቆሮንቶስ 1፥23-24)።

የክርስቶስ ሞት እግዚአብሔር ጻድቅነቱ ሳይዛነፍ፣ በፍቅሩ ኅጢአተኞችን ከቁጣው የሚያድንበት የጥበቡ መገለጫ ነው።