ወርቅ፣ ከርቤ፣ እና ዕጣን | ታሕሳስ 14

ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው። ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት።

የማቴዎስ ወንጌል 2፥10-11

እግዚአብሔር አንዳች ነገር እንደሚጎድለው በሰዎች እጅ አይገለገልም (ሐዋርያት ሥራ 17፥25)። የሰብዓ ሰገል ስጦታዎች የቀረቡለት እርዳታ ስለሚያሻው ወይም የሚጎድለው ነገር ስለነበር አይደለም። የሌላ አገር እንግዶች ወደ አንድ ንጉሥ ሲመጡ የእርዳታ ጥቅል ይዘው ቢመጡ የንጉሡን ክብር ያሳጣሉ።

አልያም ደግሞ እነዚህ ስጦታዎች በጉቦ መልክ የቀረቡ አልነበሩም። ዘዳግም 10፥17 ላይ በግልጽ የሚነግረን እግዚአብሔር መማለጃን የሚቀበል አምላክ አለመሆኑን ነው። ታዲያ ትርጉማቸው ምንድን ነው? እንዴት ነው አምልኮ የሚሆኑት?

ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለቻሉ ባለጠጋ ሰዎች የሚሰጥ ስጦታ የሚያስተጋባው፣ ሰጪው ለሰዎቹ ያለውን ክብር እና አድናቆት ነው። በአንድ መልኩ ለክርስቶስ ስጦታ መስጠት ማለት እንደ መፆም ሊታይ ይችላል። መፆም ማለት አንድን ነገር በመተው ክርስቶስ ከዚያ ከምንተወው ነገር ይልቅ የላቀ ዋጋ እንዳለው ማሳየት ማለት ነው።

ለክርስቶስ እንዲህ ያለ ስጦታ ስትሰጡ፣ ስታሳድዱ የነበረው ደስታ እርሱ እንደሆነ ትናገራላችሁ። ማቴዎስ 2፥10ን ልብ በሉ፦ “ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው”። የማሳድደው ደስታ ከአንተ ጋር ነግጄ በማተርፈው ላይ ወይም የምቀበልህ ክፍያ ላይ የተመረኮዘ ከንቱ ተስፋ አይደለም። ወደ አንተ ስመጣ አንተኑ እንጂ ከአንተ የማገኛቸውን ነገሮች ፈልጌ አልመጣሁም። ይህን ፍላጎቴን ይበልጥ ለማቀጣጠል እና ለአንተ ለማሳየት ስል ደግሞ በእጄ ያሉ ነገሮችን አሳልፌ በመስጠት በአንተ የበለጠ ለመደሰት እተጋለሁ። ለአንተ የማያስፈልግህን እኔን ግን የሚያረካኝን ነገር አሳልፌ በመስጠት፣ ሀብቴ አንተ መሆንህን እና እነዚህ ነገሮች አለመሆናቸውን በሙሉ ልቤ አውጃለሁ።

እግዚአብሔርን በወርቅ፣ በከርቤ፣ እና በዕጣን ማምለክ ማለት ይህ ይመስለኛል። እነዚህም ሆኑ ሌሎች ለእግዚአብሔር ልንሰጥ የምናስባቸው ነገሮች ሁሉ አምልኮ ናቸው።

እግዚአብሔር በልባችን ውስጥ ለክርስቶስ ያለንን ፍላጎት ያቀጣጥልልን። ከልባችን በመነጨ ደስታ እንዲህ እንበል፦ “ጌታ ኢየሱስ፣ አንተ የእስራኤል ንጉሥ የሆንከው መሲሑ ነህ። ነገሥታት ሁሉ በፊትህ መጥተው ይሰግዳሉ። አንተ እንድትመለክ እግዚአብሔር ዓለምን ሁሉ ወደፈቀደበት ይመራል። ስለዚህም ምንም ዐይነት ተግዳሮት ቢያጋጥመኝ ሥልጣንህን በመቀበል፣ ክብርን ለአንተ በማስገባት፣ አንተ ብቻ ነህ ልቤን የምታረካልኝ በማለት ስጦታዎቼን በፊትህ አቀርባለሁ።”