“ይህ ጤናማ ትምህርት ቡሩክ እግዚአብሔር ለእኔ በዐደራ ከሰጠኝ የክብር ወንጌል ጋር የሚስማማ ነው።” (1ኛ ጢሞቴዎስ 1፥11)
በ1ኛ ጢሞቴዎስ ውስጥ የምናገኘው ይህ አንጀት አርስ አገላለጽ፣ በተለመዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መካከል የተደበቀ ነው። ነገር ግን ጠጋ ብለን ስንረዳው፣ “የደስተኛው እግዚአብሔር የክብር መልካም ዜና” ማለቱ እንደሆነ እንረዳለን። በዚህ ክፍል ላይ “ብሩክ” የሚለው ቃል የዋለው የተባረከ ለማለት ሳይሆን ከደስተኝነቱ ጋር በተያያዘ መልኩ ነው።
የእግዚአብሔር ክብር በዋናነት ደስታው ነው።
እግዚአብሔር ያለ ገደብ ደስተኛ ሳይሆን በሙላት መክበሩ ለሐዋርያው ጳውሎስ የማይታሰብ ነው። ያለ ገደብ የከበረ ነው ማለት፣ ያለ ገደብ ደስተኛ ነው ማለት ነው። ሐዋርያው “የደስተኛው የእግዚአብሔር ክብር” የሚለውን ሐረግ የተጠቀመበት ምክንያት እግዚአብሔር ደስተኛ መሆኑ በራሱ የከበረ ነገር ስለሆነ ነው።
የእግዚአብሔር ክብር ልንረዳው ከምንችለው በላይ በደስተኝነቱ ዙሪያ ያጠነጠነ ነው። በአሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ታወቂው ሰባኪ ጆናታን ኤድዋርድስ እንዲህ ይላል፦ “የእግዚአብሔር ሙላት በአንድ መልኩ ከእርሱ ወደ ሌሎች የሚተላለፈው ደስታው ነው። ይህ ደስታ ደግሞ በራሱ ደስ መሰኘትና ሐሴት ማድረግ ሲሆን፣ የፍጥረትም ደስታ ማዕከል ይህ ነው።”
ይህ የወንጌል ቁልፍ አካል ነው። ጳውሎስ ሲናገር፣ “ደስተኛ የሆነው እግዚአብሔር የክብር ወንጌል” ይለዋል። እግዚአብሔር በደስታ መክበሩ የምስራች ነው። ከጨለምተኛ እና ደስተኛ ካልሆነ አምላክ ጋር ዘላለሙን ማሳለፍ የሚፈልግ ማንም የለም።
የእግዚአብሔር ደስታ የከበረ ካልሆነ፣ የወንጌል ግብ የሆነው ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም መኖርም ደስ የሚያሰኝ ነገር አይሆንም። ይህ ማለት ደግሞ ወንጌል የሚባል ነገር ከነጭራሹ የለም ማለት ነው። ነገር ግን እውነታው፣ ኢየሱስ፣ “ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” ብሎ ሲናገር ደስተኛ ከሆነው አምላክ ጋር ዘላለምን እንድናሳልፍ እየጋበዘን ነው (ማቴዎስ 25፥23)።
በዮሐንስ ወንጌል 15፥11 ላይ ኢየሱስ ሲናገር፣ “ደስታዬ በእናንተ እንዲሆንና ደስታችሁም ሙሉ እንዲሆን ይህን ነግሬአችኋለሁ” ይላል። ኢየሱስ ያስተማረው፣ የኖረው እና የሞተው የእግዚአብሔር ደስታ በእኛ እንዲሆን፣ ደስታችንም ሙሉ ይሆን ዘንድ ነው። ስለዚህም ወንጌል፣ “የደስተኛው እግዚአብሔር የክብር ወንጌል” ነው።