የተከለከለና የተሰጠ ጸጋ | ጥር 7

“ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት በብዙ መከራ ማለፍ አለብን።” (ሐዋርያት ሥራ 14፥22)

የውስጣዊ ጥንካሬ አስፈላጊነት የሚመነጨው ዕለት ተዕለት ከሚያሟጥጠን ውጥረት ብቻ ሳይሆን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሚመጡ መከራዎች እና ችግሮችም ጭምር ነው። በርግጥም ደግሞ ይመጣሉ።

በመንግሥተ ሰማይ ጉዞ መሃል ባለ የልብ ዝለት ላይ መከራ መጨመሩ የማይቀር ነው። ሲመጣም ደግሞ ልብ ይናወጣል፣ ወደ ህይወት የሚወስደው ጠባብ መንገድ ከባድ መስሎ ሊታይ ይችላል። ያረጀውን መኪና ጥንካሬ እስከ አቅሙ ጥግ የሚፈትኑ ጠባብ መንገድ እና ገደላማ ኮረብታዎች መኖራቸው በጣም ከባድ ያደርገዋል። ታዲያ ግን መኪናው ሲበላሽ ምን እናድርግ?

ጳውሎስ በሕይወቱ ውስጥ ባጋጠመው መከራ ምክንያት ሦስት ጊዜ እየጮኸ ይህን ጠይቋል። የሥጋው መውጊያ ከእርሱ እንዲወገድለት ለምኗል። የእግዚአብሔር ጸጋ ግን በሌላ መልክ እንጂ በጠየቀው መልክ አልመጣም። ክርስቶስ እንዲ ብሎ መለሰለት፣ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” (2ኛ ቆሮንቶስ 12፥9)።

እዚህ ጋር፣ እፎይታ በሌለው መከራ ውስጥ፣ ጸጋን፣ በክርስቶስ የማጽናት ኃይል መልክ እናየዋለን – በአንዱ ጸጋ መከልከል ውስጥ ሌላ ጸጋ ተሰጥቷል ማለት እንችላለን። ጳውሎስም ይህን የወደፊት ጸጋ መሟላት በማመን ምላሽ ይሰጣል፦ “ስለዚህ የክርስቶስ ኀይል በእኔ ያድር ዘንድ፣ ይበልጥ ደስ እያለኝ በድካሜ እመካለሁ” (2ኛ ቆሮንቶስ 12፥9)። ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔር “በተከለከለ ጸጋ” ውስጥ ሌላ ጸጋ ይሰጠናል።

አንዴ የገጠመኝን ልንገራችሁ። አንድ ወቅት እጅግ በጣም ሞቃታማ በሚባል ጊዜ እና አካባቢ፣ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ በመኪና ጉዞ እያደረግን፣ በድንገት የመኪናችን የውሃ ፓምፕ ተበላሽቶ እዚያ ሙቀት ላይ ጸጥ አለ። ከየትኛውም ከተማ 32 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ሆነን አውላላ ሜዳ ላይ ቆመን ቀረን።

ያን ጠዋት መኪናው በትክክል እንዲሠራ እና ወዳሰብንበት በሰላም እንድንደርስ ጸልዬ ነበር። ከዚያ ግን መኪናችን ተበላሸ። ችግር የሌለበት የጉዞ ጸጋ ጠይቀን ነበር፤ ተከለከልን። በአጠገባችን የሚያልፍ የትኛውም መኪና አልቆመልንም ነበር። ከዚያም ልጄ አብርሃም (በዚያን ጊዜ 11 ዓመቱ ነበር) “አባባ፣ እንጸልይ” አለኝ። ስለዚህ ከመኪናው ጀርባ ተንበርክከን ከእግዚአብሔር በሚያስፈልገን ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ የወደፊት ጸጋን ጠየቅን። ቀና ብለን ስንመለከት አንድ ፒክ አፕ መኪና ቀስ ብሎ ዳሩን ያዘ።

ሹፌሩ ካለንበት ቦታ 32 ኪ.ሜ. አካባቢ ራቅ ብሎ የሚሠራ መካኒክ ነበር። ሄዶ የሚያስፈልጉትን ዕቃዎች በማምጣት መኪናውን ለመጠገን ፈቃደኛ እንደሆነ ነገረን። ከዚያም ከእርሱ ጋር አብሬ ወደ ከተማ እየሄድኩ ወንጌል ሰበኩለት። በአምስት ሰዓታት ውስጥ ሁሉንም ጨርሰን መንገዳችንን ቀጠልን።

ታዲያ ከጸሎታችን መልስ አስደናቂ የሆነው ነገር በተከለከለ የጸሎት መልስ መካከል ጸጋ መምጣቱ ነው። ምንም ችግር የሌለበት ጉዞ ጠየቅን። እግዚአብሔር ችግር ሰጠን። ነገር ግን በተከለከለ ጸጋ መካከል፣ ሌላ ጸጋ አገኘን። አኔም ከዚያን ቀን ጀምሮ ጠቢቡ እግዚአብሔር ለእኔ፣ ለማያምኑ መካኒኮች፣ እና ቆመው ለሚመለከቱን የ11 ዓመት ልጆች የሚበጀውን ጸጋ እንደሚሰጥ ማመንን መለማመድ ጀመርኩ። እግዚአብሔር እንዲያስቀርልን በጠየቅነው መከራ ውስጥ ድንቅ ጸጋን ሲሰጠን አዲስ ሊሆንብን አይገባም። ለራሱ ክብር እና ለእኛ ጥቅም ሲል ጸጋውን እንዴት እንደሚያከፋፍል ጠንቅቆ ያውቃል።