“ወደ እኔ ተመልከት፤ ማረኝም፤ ለባሪያህ ኀይልህን ስጥ፤ የሴት ባሪያህንም ልጅ አድን።” (መዝሙር 86፥16)
በመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ውስጥ፣ ከመዝሙረኞቹ የማያቋርጥ ልመና መካከል ዋነኛው የእግዚአብሔር የወደፊት ጸጋ ነው። ለሚያስፈልጋቸው ለእያንዳንዱ ነገር የእግዚአብሔር ጸጋ እንዲሰጣቸው ደጋግመው በጸሎት ይለምናሉ። ለአስፈልጎቶቻችን ሁሉ በወደፊቱ ጸጋ ላይ ዕለት ተዕለት ስለመደገፍ መልካም ምሳሌም ይሰጡናል። እስቲ ጩኸታቸውን እናዳምጥ፦
- እርዳታ ሲያስፈልጋቸው ለጸጋ ጮኸዋል፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ስማ፤ ማረኝም፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ረዳት ሁነኝ” (መዝሙር 30፥10)።
- በድካማቸው ጊዜ፦ “ወደ እኔ ተመልከት፤ ማረኝም፤ ለባሪያህ ኀይልህን ስጥ” (መዝሙር 86፥16)።
- ፈውስ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐቅመ ቢስ ነኝና ማረኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐጥንቶቼ ተናግተዋልና ፈውሰኝ ” (መዝሙር 6፥2)።
- ጠላቶች ሲያሰቃዩአቸው፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ጠላቶቼ የሚያደርሱብኝን መከራ ተመልከት፤ አይተህም ራራልኝ፤ ከሞት ደጅም አንሥተህ መልሰኝ” (መዝሙር 9፥13)።
- በብቸኝነታቸው ጊዜ፦ “እኔ ብቸኛና የተጨነቅሁ እንደ መሆኔ፣ ወደ እኔ ተመለስ፤ ምሕረትም አድርግልኝ” (መዝሙር 25፥16)።
- እጅግ ባዘኑ ጊዜ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ በመከራ ውስጥ ነኝና ማረኝ፤ ዐይኖቼ በሐዘን ደክመዋል፤ ነፍስና ሥጋዬም ዝለዋል” (መዝሙር 31፥9)።
- ኃጢአት በሠሩ ጊዜ፦ “እኔም፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረት አድርግልኝ፤ አንተን በድያለሁና ነፍሴን ፈውሳት” (መዝሙር 41፥4)።
- የእግዚአብሔር ስም በሕዝቦች መካከል ከፍ እንዲል በተመኙ ጊዜ፦ “እግዚአብሔር ይማረን፤ ይባርከን፤ ፊቱንም በላያችን ያብራ፤… መንገድህ በምድር ላይ፣ ማዳንህም በሕዝቦች ሁሉ መካከል ይታወቅ ዘንድ” ብለው ጮኸዋል (መዝሙር 67፥1-2)።
በማያሻማ ሁኔታ፣ ጸሎት በቅዱሳን ነፍስ እና ወደፊት በሚገለጠው የጸጋ ተስፋ መካከል ያለ ታላቅ የእምነት ሠንሰለት ነው። አገልግሎታችን በእግዚአብሔር የሚጸናው እና የሚበረታው በጸሎት ከሆነ፣ በእርግጥ የሚጸናው በወደፊቱ ጸጋ ላይ ባለ እምነት ነው ማለት ነው።