ለአዲሱ ዓመት የተሰጠ ጸጋ | መስከረም 1

ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ አሁን የሆንሁትን ሆኛለሁ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋ ከንቱ አልሆነም፤ እንዲያውም ከሁሉም በላይ በትጋት ሠርቻለሁ፤ ዳሩ ግን እኔ ሳልሆን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥10)

ጸጋ ማለት መልካም ነገር በማይገባን ጊዜ፣ እግዚአብሔር ለእኛ መልካምነት ለማሳየት መፈለጉን የሚያመላክት ብቻ አይደለም። ይልቅ የሚሠራ፣ በሕይወታችንም ውስጥ መልካም ነገሮች እንዲከስቱ የሚያደርግ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ እውነተኛ ኅይል ነው።

ጳውሎስ እንዲተጋ በውስጡ ሲሠራ የነበረው ያ የእግዚአብሔር ሥራ፣ የእግዚአብሔር ጸጋ ነበር፦ “በእግዚአብሔር ጸጋ… ከሁሉም በላይ በትጋት ሠርቻለሁ” ይለናል። ስለዚህ ጳውሎስ፣ “የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤” ደግሞም በመቀጠል “እንደ በጎ ፈቃዱ መፈለግንና ማድረግን በእናንተ ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና” ይላል (ፊልጵስዩስ 2፥12-13)። ጸጋ፣ በእኛና ለእኛ መልካም ነገሮችን የሚያደርግ የእግዚአብሔር ኅይል ነው።

ይህ ጸጋ ቀድሞ የነበረ፣ ወደፊትም የሚኖር ነው። ይህ ጸጋ የማያቋርጥ ጅረት ነው። ትናንት የነበረ፣ ዛሬም ያለ፣ ወደ ፊትም የሚኖር ነው።

ትናንት ተከማችቶ በነበረው ጸጋ ላይ፣ ሌላ በላያችሁ እየፈሰሰ የሚያበረታችሁን ጸጋ ዛሬ ትቀበላላችሁ። ትናንት ለተቀበላችሁት ጸጋ ተገቢው ምላሽ ምስጋና ነው፤ ወደፊት ተስፋ ለተገባላችሁ ጸጋ ትክክለኛው ምላሽ እምነት ነው። ባለፈው ዓመት ላየነው ጸጋ አመስጋኝ ነን፤ ለአዲሱ ዓመት ደግሞ ወደ ፊት ሊገለጥ ባለው ጸጋ ላይ እንተማመናለን።